#Fastmereja:በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ውጤቶች ላይየሚታየውን የአእምሯዊ ንብረት ጥሰት ለመከላከልና መብቶቻቸው በሕግ እንዲጠበቁ ለማስቻል ለተከታታይ 18 ወራት ሲተገበር የቆየው ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት መጠናቀቁ ተበሰረ።
“በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ የእእምሯዊ ንብረት መብቶችን ማጠናከር” (SIPRE) በሚል መጠሪያ ሲተገበር የቆየው የዚህ ፕሮጀክት ማጠቃለያና የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የምክክር መድረክ በዛሬዉ እለት ሚያዝያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሞናርክ ሆቴል ተካሂዷል።
በሰላም ኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ ፕሮጀክቱ በዩኔስኮ የባህል ብዝኃነት ዓለም አቀፍ ፈንድ (IFCD) የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ሕብረት አማካኝነት በጋራ ሲተገበር ቆይቷል።
ባለፉት 18 ወራት ፕሮጀክቱ በስነ-ስዕል፣ በቅርጻ ቅርፅ፣ በፊልም፣ በቲያትር፣ በሙዚቃና በውዝዋዜ ዘርፎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን፤ በዋናነት በግንዛቤ ማስጨበጫ፣በክህሎት ማሳደጊያ እና በስራ ትስስር በእነዚህ በሦስት ዘርፎች ስኬቶች መመዝገባቸው ተገልጿል።
በማጠናቀቂያ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ተወካዮች እንደገለጹት፤ ምንም እንኳ የኪነ-ጥበብ ዘርፉ እያደገ ቢመጣም፣ የፈጠራ ውጤቶች ያለፈቃድ ጥቅም ላይ መዋልና የቅጂ መብት ጥሰት አሁንም በዘርፉ ላይ ትልቅ ስጋት እንደሆነ ገልፀዋል።
በመሆኑም የSIPRE ፕሮጀክት ቢጠናቀቅም፣ የተጀመሩ የንቅናቄ ስራዎች ከመንግስትና ከክልል የባህል መዋቅሮች ጋር በዘላቂነት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሰላም ኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መካከል የነበረውን የግንኙነት ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልፀዉ የኪነ-ጥበብ ስራዎች የሀገር ገጽታን ከመገንባት ባለፈ ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ወሳኝ መሆኑንም አቶ ሲሳይ አክለው ገልጸዋል።
ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለፈጠራ ባለቤቶች ተገቢው ክብርና ክፍያ እንዲሰጥ እንዲሁም ለዘርፉ እድገት ምቹ የሕግ ከባቢ እንዲፈጠር መሰረት ጥሎ እንደሚያልፍ ይጠበቃል።



Source: FastMereja








No comments yet.