በጦሩ መካከል የተሳለ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔር መልአክ አየ

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

የመጀመሪያ ስሙ ፒሉ-ፓዴር ሲሆን ቤተሰቦቹ አረማውያን ሲሆኑ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የተመለሱ ናቸው፡፡ ፊታቸው የውሻ የሆነ፣ የአውሬነት ጸባይ ያላቸው በእግዚአብሔር ኃይል የሚታዘዙት ሁለት አገልጋዮች የነበሩት አባቱ ወደ መርዶሳውያን ሀገር ተማርኮ ቢሔድም ጸጋ እግዚአብሔር በዝቶለት በዚያ ሹመት አጊቷል፡፡ ልጃቸው ቅዱስ መርቆርዮስን የወለዱት ግን በሮም ነው፡፡ ወላጆቹ ሲያርፉም የአባቱን ስልጣን ተረክቧል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በክርስቲያኖች ሁሉ ዘንድ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪካቸው ከሚነገርላቸው ሰማዕታት አንዱ ሲሆን በሀገራችን በኢትዮጵያም በአማላጅነቱ የሚታወቀው ታላቁ ሰማዕት ነው፡፡ መርቆሬዎስ ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው። በሁለተኛ ትርጉሙ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው። በሀገራችን በኢትዮጵያም በበርካቶች ዘንድ በፈጣን ተራዲኢነቱ ይታወቃል፡፡

የዓለም ክብራቸውን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ከጣሉና በተጋድሏቸው ከሚታወቁ ሰማዕታትም አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስ የአባቱን ስልጣን ወርሶ በንጉሱ ስር በመርዶሳውያን አገር ላይ ተሾመ፡፡ መርቆሬዎስ በመኰንንነት በተሾመም ጊዜ የውሻ ፊት ያላቸው የአባቱ አገልጋዮች አብረውት ነበሩ፤ ለመዋጋትም ሲወጣም እግዚአብሔር የአውሬነት ተፈጥሯቸውን ይመልስለት ስለነበር ማንም አይቋቋመውም ነበር፡፡ የድል አድራጊነት ኃይሉ ዜናም በሁሉም ሀገሮች ተሰማ፡፡ በሮሜ ሀገር ጣዖትን የሚያመልከው ዳኬዎስ የተባለውም ንጉሥ የበርበር ሰዎች ጋር ጦርነት ሊገጥም በወጣ ጊዜ እጅግ ሲበዙበት ፈራ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን በጦሩ መካከል የተሳለ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ ስላየ “እግዚአብሔር ያጠፋቸዋልና አትፍራ” አለው፤ ከዚያም ሰይፉን ለቅዱስ መርቆሬዎስ ሰጠውና “ጦርነቱን ድል ባደረግህ ጊዜ እግዚአብሔርን አስበው” አለው፡፡

ቅዱስ መርቆሬዎስ በድሉ ውስጥ ትልቅ ድርሻ በወሰደበት ውጊያም ጦርነቱ በንጉሱ ዳኪዮስ ወገን አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ መርቆሬዎስም ድል አድርጎ ሲጨርስም መልአኩ ድጋሚ ተገልጦለት “ለምን የፈጣሪህን ስም መጥራት ረሳህ” አለው፡፡ ንጉሡ ግን ከጦርነቱም በኋላ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን አደረገ፡፡ በዚህ ያዘነው ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን አልተገኘም፡፡ ንጉሡም መልእክተኞችን ልኮ አስመጣውና “ከእኔ ጋር ለምን አታጥንም?” አለው፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስ ትጥቁንና ልብሱን አውልቆ ከወረወረለት በኋላ “ክብር ይግባውና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ አልክደውም፤ ለረከሱ ጣዖቶችህም አልሰግድም” አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ በክርስትናው ተፈተነ፤ ውለታው ተረስቶ ንጉሡ በልዩ ልዩ ሥቃዮችም እጅግ አሠቃየው፡፡ ይሁንና ስለ መርቆሬዎስ ብለው የሀገሩ ሰዎች እንዳይነሡበት ፈርቶ በብረት ችንካር ቸንክሮ የቀጵዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ሆነች ወደ ቂሳርያ ከደብዳቤ ጋር ላከው፡፡

በዚያም እጅግ ካሠቃዩት በኋላ በንጉሥ ዳኬዎስ ትዕዛዝ ኅዳር 25 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት ተጋድሎውን ፈጸመ፤ በየወሩ በ25ኛው ቀንም መታሰቢያው ነው፡፡ የሕይወትንም አክሊል ተቀዳጀ፤ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነጹለት፡፡ እግዚአብሔር በሰማዕቱ ስም ካደረጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት አንዱ፣ ጌታችንን ክዶ ጣዖታትን ማምለክና ክርስቲያኖችን ማሠቃየት የጀመረው ንጉስ ዑልያኖስ የቂሳርያውን ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ባስልዮስ አስተምሮ ሊመልሰው ቢመጣ ክብር ይግባውና ጌታችንን ሰድቦ ባስልዮስንም አሠረው፡፡ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ሲጸልይም ሥዕሉ ወደ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ሄዶ በጦር ወግቶ ገደሎት ወዲያው ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ዛሬም የገዳማውያንን ጸሎት ይሰማል፡፡ ገዳማቸውን ስንደግፍ በዓታቸውን ስናጸና የበረከታቸው ተሳታፊ እንሆናለን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: