ለኮሪደር ልማት የተዘጋጀን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለውን የኤሌክትሪክ ኬብል የሰረቁ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ እጅ ከፍንጅ ተያዙ፡፡
ሦስቱ ግለሰቦች ወንጀሉን የፈፀሙት ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ስፖርት ፌደሬሽን አካዳሚ ፊት ለፊት ከጠዋቱ 4 ላይ ነው።
አስመራ ነገራ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 47749 ኢት የሆነ ክሬን ተሽከርካሪ ሹፌር፣ ኤልያስ በርሄ የሹፌሩ ረዳት እና ወርቁ ኖራህ ተባባሪ በመሆን 9 ጥቅል እና አንድ ገመድ የሌለው የኬብል መጠቅለያ አጠቃላይ የዋጋ ግምቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣና ለኮሪደር ልማት ሊዘረጋ የነበረ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ሲጭኑ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ገመዶች አስጭናችሁ አምጡ ተብለን ነው በማለት ንብረቱን ሲጭኑ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ሦስቱ ወንጀል ፈፃሚዎች ከነተሽከርካሪው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የአደይ አበባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገ ተጨማሪ ምርመራ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት ሰራተኞች አለመሆናቸው ተረጋግጧል።
ወንጀል ፈፃሚዎቹ እጅ ከፍንጅ እንዲያዙ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ፖሊስ ገልፆ የወንጀል ፈፃሚዎች መያዝ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ያለው ቁርኝት ይበልጥ እየጠነከረ መምጣቱን ጥሩ ማሳያ እንደሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል፡፡ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ ምስጋና የሚቸረውና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን ዋና ጠቅላይ መምሪያው አስታውቋል፡፡
Addis Ababa police



Source: Yeneta Tube









No comments yet.