ዩናይትድ ስቴትስ በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል ማለፍ ላልቻሉ የንግድ መርከቦች የጀመረችውን አጀብ ለጊዜው እንደምታቆም አስታወቀች። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመርከቦች እጀባው የቆመው ከኢራን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለን ፍላጎት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን በቅርብ ቀናት በሰርጡ ግጭቶች የነበሩ ቢሆንም ትራምፕ ግን ወደ ስምምነት የሚያመራ ትልቅ ለውጥ ላይ ተደርሷል ብለዋል። መርከቦችን የማጀቡ ዘመቻ የሰላም ስምምነቱ ሊጠናቀቅና ሊፈረም ይችል እንደሆነ ለማየት ለአጭር ጊዜ ይቆማል ሲሉም ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህን ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ የምታካሂደውን የማጥቃት ዘመቻ ማጠናቀቋን ትናንት ከተናገሩ በኋላ ነው። ይሁንና ሩብዮ ኢራኖች በሰርጡ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ለሚሰነዝሩት ማንኛውም አዲስ ጥቃት ግን ከባድ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው አስጠንቅቀዋል።
ኢራን በበኩልዋ የሰላም ስምምነቱን የምትቀበለው አድሏዊ ካልሆነ ብቻ ነው ስትል አስታውቃለች። ለጊዜው እንደሚቋረጥ ዛሬ የተነገረው እጀባ ለሦሶት ቀናት ብቻ ነበር የዘለቀው። «የነጻነት ፕሮጀክት» የሚል ስያሜ የተሰጠው ይኽው ዘመቻ በሆርሙዝ ሰርጥ የመርከቦች ጉዞ እንዲቀጥል የሚያደርግ ጉልህ ውጤት አለማስገኘቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
DW Amharic

Source: Yeneta Tube









No comments yet.