#FastMereja I ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞቹ በማያውቋቸው ዓለም አቀፍ ስልኮች አማካኝነት ለከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና ለማጭበርበር ድርጊት እንዳይጋለጡ አስቸኳይ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ። አጭበርባሪዎቹ ደንበኞች ተመልሰው እንዲደውሉ በማድረግ ከፍተኛ የውጭ አገር ጥሪ ክፍያ (International Tariff) እንዲቆረጥባቸው የሚያደርግ ስልት እየተጠቀሙ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ተዋናዩ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ግለሰቦች በማያውቋቸው የውጭ አገር ስልክ ቁጥሮች አማካኝነት “Missed Call” ወይም የጥሪ ምልክት በማድረግ ደንበኞች ተመልሰው እንዲደውሉ የማሳሳት ስራ እየተሰሩ ይገኛሉ።
እንደ ተቋሙ ገለጻ፣ በተለይም በ +601፣ +993፣ +371፣ +370፣ +255፣ +375፣ እና +381 መሪ ኮዶች የሚጀምሩ ስልኮች ለማጭበርበሪያነት በስፋት እየተዋሉ መሆኑ ተለይቷል። ደንበኞች ለእነዚህ ጥሪዎች ምላሽ በሚሰጡበት ወይም ተመልሰው በሚደውሉበት ወቅት፣ ጥሪው የሚታሰበው በዓለም አቀፍ ከፍተኛ ታሪፍ በመሆኑ በሂሳባቸው ላይ ያለውን የገንዘብ መጠን ወይም የአየር ሰዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይበላል።
ይህ አይነቱ ማጭበርበር በዓለም አቀፍ ደረጃ “Wangiri Fraud” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አጭበርባሪዎቹ ከቴሌኮም ኦፕሬተሮች ጋር በሚኖራቸው የገቢ ክፍፍል ስምምነት ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለማያውቃቸው የውጭ አገር ጥሪዎች ተመልሶ በመደወል አላስፈላጊ ለሆነ ኪሳራ እንዳይጋለጥ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
Source: FastMereja









No comments yet.