በወላይታ ዞን ባይራ ኮይሻ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት የሆነውን የ”ስንዴ ነዶ” ባነር ቀድዶ የጣለው ተከሳሽ በ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት።
ተከሳሽ አቶ በላቸው ባሳ በቀን 06/09/2018 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ገደማ በባይራ ኮይሻ ወረዳ “ጠካቻ ቀጠና 1” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሰቅሎ የነበረን የፓርቲውን የምርጫ ቅስቀሳ ባነር ቀድዶ በመጣል ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች እጅ ከፍንጅ ተይዟል።
በወረዳው ፖሊስ ምርመራው በአስቸኳይ ተጠናቅቆ የቀረበለት ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተ ሲሆን ተከሳሹ በ2011 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162 አንቀጽ 158ን በመጣስ ወንጀል መፈጸሙን የሚያስረዱ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ተከሳሹ የቀረበበትን የጥፋተኝነት ክስ አምኖ በችሎት ቃሉን ሰጥቷል።
የባይራ ኮይሻ ወረዳ ፍርድ ቤት መዝገቡን መርምሮ ድርጊቱ መፈፀሙን በማረጋገጡ ተከሳሹን የሚያርምና ሌሎችም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጽሙ የሚያስተምር መሆን አለበት በማለት ተከሳሹ በ5 ወር እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
ምንጭ:- የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ህዝብ ግንኙነት ክፍል









No comments yet.