”ማንቺስተር ያሸነፈ ቀን !”

- Advertisement -
Sidebar AD

ትናንት አርሰናል አሸነፈ! በህይወቱ ሙሉ ሲመኘው የነበረውን ይህን ድል ቆሞ ማየት የነበረበት አንድ ሰዉ ነበር።

ብዙ ጊዜ ማንቺስተር አሸንፎ ደጋፊዎቹ መሬት አልበቃቸው ብሎ ሳይ እንደሁሌውም ትዝያለኝ ያ ራሱን ‘የአርሰናል ቁልፍ ሰው’ አድርጎ ይቆጥር የነበረው ታናሽ ወንድሜ ነው

በፍቃዱ ብርሃኑ ይባላል… እማዬ “ፍቃዴ” ትለው ነበር፡፡ እኔን ጨምሮ እሱን የሚያውቁት ሁሉ “ፍቄ” ብለው ነበር የሚጠሩት፡፡ በህጻን አዛውንቱ ተወዳጅ የነበረ ወንድሜ …. ዛሬ በህይወት የለም።

ፍቄ ሁሌም ማታ የጠንቋይ መጣፍ የመሰለ ደቃቅ ጽሁፍ የታጨቀበትን ሊብሮ ጋዜጣ ይዞ ወደቤት ይመጣል። ገና ጎረምሳ ነው፡፡ ረጅም …1 ሜትር ከ87 ሳ.ሜ ቁመቱን በአሮጌው ሶፋ ላይ ዧ አድርጎ እንሩን አንፈራጦ ይቀመጥና …. ፊቱን ጋዜጣው ውስጥ ቀብሮ …ኮስተር ፈታ እያለ ‘የነቡናን እና የነአርሴን’ ወግ ይጨመጭማል።

“… ምንድነው ግን የምታነበው?” ትለዋለች እማዬ፡፡ ”ስፖርት ነው እማ.. ብዙም አታውቂውም” ይላታል።

”ኡኡቴ! አዋቂ ነኝ ብለህ ሞተሃል..ደሞ ለቅሪላ ወሬ!” ትላለች።

” ጭንቅላትህን በኳስ ዕወቀት ከምትሞላ ትምህርትህ ላይ አትበረታም ነበር? …ደደብ!! …ነገ አርሰናል መጥቶ ይፈተንልህ መሰለህ? ..” ብዬ ልጮህበት እፈልጋለሁ።

ግን ብዙ ጊዜ ይህንን ብዬው ጉሮሮዬን አመመኝ እንጂ ያመጣሁት ለውጥ የለም።

እማዬ ማለዳ ወደቤተክርስቲያን በምትሄድባቸው ቀናት ወደእግዜር ከምትወስደው የራሷ ጥያቄዎች በተጨማሪ ፍቄ የሚያዛት ተጨማሪ ፀሎት አለ። ጨዋታ ያለ ቀን ወይ ቡና… ወይ አርሰናል እንዲያሸንፍ እንድትጸልይለት ይነግራታል፡፡

የሆነ ጊዜ የቡና ረከቦቷን የምትሸፍንበትን ጨርቅ አነስቶ ጥሎ በምትኩ ሁለት የቡና አርማ ያለበትን ባንዲራ አሰርቶ አመጣና አንዱን “የቡና ስኒ በቡና አርማ ነው መሸፈን ያለበት” ብሎ ሰጣት፡፡ አንዱን ደግሞ የቤታችን ግድግዳ ላይ በሚስማር መትቶ ሰቀለው፡፡ ቤት ስገባና የሆነውን ሳይ ተናደድኩና ገንጥዬ ጣልኩበት፡፡ የረከቦቱን ግን እማዬ ከለከለችኝ፡፡ “ይሁን፣በገዛ ሲኒዬ ምን አገባህ” ብላ ፡፡ እነዚያ ጨርቆች ዛሬም ድረስ ቤታችን አሉ፡፡

እማዬን “ እሙ!” ነበር የሚላት፡፡ የሚተኛው ከሷ ጋር ነው፡፡ የመጨረሻ ልጅ ስለሆነ ነው መሰለኝ እንደነፍሷ ትወደዋለች፡፡ ጨዋታ ያለ ቀን ታዲያ እማዬ ማለዳ ወደቤተክርስቲያን ለመሄድ ስትነሳ የተሸፈነበትን ብርድልብስ ገለጥ ያደርግና “እሙ! ዛሬ የኔ ቡድን ይጫወታል።እንዲያሸንፍ ጸልዪልኝ …ካሸነፍን ስለት ታስገቢልኛለሽ! ” ይላታል፡፡

“አይ እዳዬ!….. ደሞ ዛሬ አቡነ ተክለሃይማኖት እንዴት ያረጉኝ ይሆን” ትላለች ። እማዬ ስትምልም ስትለምንም በአቡነ ተክለሃይማኖት ነው፡፡

አንድ ቀን ‘የምር ስለሱ ኳስ ጨዋታ ትጸልያለሽ?’ ብዬ ጠየቅኳት፡፡ “እንዴ አዎና!…ተክልዬ !! የዚህን ልጅ ልብ የበሉት ባለኳሶች እንዲያሸንፉ እርዱልኝ…..ጉድ እንዳይሰሩኝ ኋላ! እላቸዋለሁ” አለችና አሳቀችኝ።

ምን ታድርግ? የርሱ ክለብ የተሸነፈ’ለታ ቤታችን የሚፈጠረውን ነገር ስለማውቅ አልፈረድኩባትም፡፡

ጨዋታ ያለ ቀን ገና በጠዋቱ አጠገቤ ቆም ይልና…”መላ’ዬ …ጨዋታው 3 ከ 45 ይጀምራል። ከዚያ በፊት ሃይላይት አለ። ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ ያልቃል። እንደጨረስኩ ወዲያው እመጣለሁ።” ይላል።

ማስፈቀዱ ነው፡፡ ዝም እላለሁ።ቆሞ ያየኛል።ዝም እላለሁ። አይሄድም፡፡ እኔ ጥዬው እሄዳለሁ።

አንዳንዴ የሆነ ልቡን ስልብ አድርጎ ራሱን የሚያስተው ነገር አለ፡፡ ሲጨነቅ ወይም ሲበሳጭ እንዲያ ይሆናል፡፡

አርሰናል የተሸነፈ’ለት ታዲያ ብዙ ጊዜ ያ ህመም ይነሳበታል፡፡ ቤት እንደገባ በዚያ ቁመቱ ሶፋ ላይ ዧ ብሎ ይወድቃል፡፡ ጸጥ ነው የሚለው፡፡ አንዳንዴ ሞተ ብለን የምንጮህበት ቀን አለ።ውሃም ጸበልም ደፋፍተንበት ነፍስ ከዘራ በኋላ “ደህና ነኝ እኮ” ሲል ደግሞ የኔ ንዴት በተራው አናቴ ላይ ይወጣል።

“አንተ በማይረባ ኳስ እየመጣህ ትዘረጋለህና እኛ መጨነቅ አለብን?” ብዬ እጮህበታለሁ፡፡ መልስ አይሰጠኝም፡፡ሌላ ቀንም እንዲሁ ይሆናል፡፡

የሆኑ ከሌላ ሰፈር የሚመጡ የጊዮርጊስ ይሁኑ የማንቺስተር ደጋፊዎች እሱን ሁሌም እንደተቃረኑት ነበር። ኳስ የሚያዩት አብረው መሰለኝ ፡፡

ጨዋታ ያለ ቀን ታዲያ…ብዙ ጊዜ እኩለ ሌሊት ከእንቅልፌ የሚያባንነኝ በራችን አቅራቢያ የምሰማው የብዙ ልጆች ዘፈን የሚመስል ጫጫታ ነበር። እኛ ቤት በር ላይ አርሰናልን የሚሳደብ ዘፈን ከሰማሁ በቃ ነገር አለ ማለት ነው !።

ፍቄን ለማብሸቅ የሚዘፈን ዘፈን መሆኑን አውቃለሁ።
ልጆቹ የሚሉት ነገር አይገባኝም። ግን ሁለቱ ቡድኖች ከማንም ጋር ይጫወቱ ብቻ አርሰናል ከተሸነፈ ወይም ማንቺስተር ካሸነፈ እሱን ለማብሸቅ እኩለ ሌሊት በራችን ላይ ይመጡና ይጨፍራሉ።

አንድ ቀን ከነሱ ጋር ሲደባደብ ፖሊሶች ደረሱና ብዙዎቹን ያዟቸው፡፡ እሱንም ይዘውት መኪና ላይ ከጫኑት በኋላ የኔ ወንድም መሆኑን ሲነግራቸው ደውለው ጠርተውኝ ፊቴ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ለቀቁት፡፡ ለእማዬ ብዬ እንጂ እስር ቤትን ትንሽ ቢቀምሳት ቅር አይለኝም ነበር፡፡

እሱ የሚደግፈው ቡድን ያሸነፈ’ለት ደግሞ ታሪክ ይገለበጣል፡፡እማዬ ይህንን ስትሰማ ወደሰማይ እያንጋጠጠች “ዛሬስ ተክለሃይማኖት ገላገሉኝ !” ትላለች።

የዚያን ቀን ታዲያ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ አይወስደውም። ብቻውን ይስቃል። አልጋው ራስጌ ፎቷቸውን የሰቀለውን ማንነታቸውን የማላውቃቸውን ተጨዋቾች በተኛበት አንጋጦ ያያቸዋል፡፡ ጸጥ ባለው ሌሊት ድንገት ይነሳና “ይሄ የተረገመ ልጅ! ሰራላቸው እኮ!” ብሎ በሳቅ ፍርስ ይላል።

አንዳንዴ ዝም ብዬ ሳየው ጤነኛ ሁሉ አይመስለኝም ነበር ።እማዬ ግን “ተወው ልጅ አይደል? ብቻ አይመመው እንጂ ሲለፈልፍ ቢያድር እኔ ምን ቸገረኝ…ሲያድግ ይተወዋል” ትላለች፡፡

ፍቄ ገና በ21 ዓመቱ አንድ እሁድ ቀን ድንገት ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡ ሆስፒታል በገባ በሶስተኛ ቀኑ …እኛንም የሚወዳቸውን ቡናና አርሰናልንም ሳይሰናበት በዚያው ሄደ።

የቀብሩ ዕለት የነበረው ህዝብ ብዛት እስካሁን ሳስበውም ይገርመኛል። በዚያ እድሜው ትምህርቱን ትቶ በሚሰራው ስራ የሚያገኘውን ደመወዝ ሁሉ የሰፈር አቅመደካሞችን ፣ ልጅ ያላቸው የኔ ቢጤዎችን ወዘተ በቋሚነት ይረዳበት እንደነበር ያወቅኩት የለቅሶው ሰሞን ሰዎች ስለርሱ ሲያወሩ በሰማኋቸው ታሪኮች ነው፡፡

በስሙ ትልቅ የእግር ኳስ ግጥሚያ ተዘጋጅቶለትም ነበር፡፡ የዋንጫው ቀን አሸናፊውን ቡድን ስሸልም ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር ፡፡

አሁንም ታዲያ ኳስ በሚታይባቸው ቤቶች በኩል ሳልፍ የደጋፊዎችን ጩኸት ስሰማ ፊቴ ላይ ድቅን የሚልብኝ አሱ ነው ። ምን ያደርጋል ያንን ምድር የማይበቃው የሚመስል ዋልያ …ያች ቀዝቃዛ ቀን እንደዋዛ ይዛው ሄደች….የርሱ መጉደል በቤታችን ይዞት የመጣው ከባድ ሃዘን እናቴን ህመምተኛ አድርጓት ኖሯል፡፡ ባሰብኩት ቁጥር የሚናፍቀኝ ከፊቱ የማይጠፋው ፈገግታ ነው፡፡

ፍቄ ወንድሜ ! ….ነፍስህ በሰላም ትረፍ !!

የሚናፍቅህ ወንድምህ
መላኩ ብርሃኑ




Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2