በሙስና የወንጀል ድርጊት የተከሰሱ በእስራት ተቀጡ

- Advertisement -
Sidebar AD

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች የቀድሞ ዳይሬክተርን ጨምሮ 7 ግለሰቦች በተከሰሱበት የማይገባ ጥቅምን በማግኘት የወንጀል ድርጊት በእስራት ተቀጡ።

ግለሰቦቹ በዜግነት ኤርትራዊት የሆነች ግለሰብ ኢትዮጵያዊት ናት በማለት 400 ሚሊየን ብር የሚገመት ቤት እንድታገኝ ለማድረግ በመደራደራቸው ከ2 እስከ 7 ዓመት በሚደረስ ጽኑ እስራት እና በገንዘብ ቅጣት ተቀጥተዋል፡፡

ተከሳሾች 1ኛ አቶ ሙልዬ ወለላው የፌዴሬሽን ም/ቤት የህገ መንግሥት ትርጉምና የሕጎች ሕገ መንግሥታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረ፣ 2ኛ አቶ ኃ/ሚካኤል ልኬ የህግ አማካሪ እና ጠበቃ፣ 3ኛ አቶ ቃላት ባህታ በግል ስራ የሚተዳደርን ጨምሮ 7 ግለሰቦች ናቸው፡፡

በመጀመሪያ ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) (ሀ) እና (2) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ነው፡፡

1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር የማይገባቸውን ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘትና ለሌሎችም ለማስገኘት በማሰብ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ የሀገር ደህንነትን እና ህልውናን ለማስጠበቅ ሲባል ከሀገር የተሸኙ ኤርትራዊያን ንብረቶችን በጨረታ እንዲሸጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከሀገር እንዲወጡ በተደረጉት ኤርትራዊ ቦሌ ክ/ከ ወረዳ 3 ስር የሚገኝ መኖርያ ቤት እና ይዞታ ለጨረታ እንዲቀርብ ተደርጎ 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር ወ/ሮ አልጋነሽ ኃይሉ የጨረታው አሸናፊ በመሆን በ1992 ዓ.ም የሽያጭ ውል በመፈፀም ቤቱን ከተረከቡ በኋላ ተከሳሾች በሀሰተኛ ደብዳቤው መነሻነት በዜግነት ኤርትራዊት የሆነችው 4ኛ ተከሳሽ ኢትዮጵያዊ ናት በሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ ውሉ ፈርሶ ቤቱን ወ/ሮ አልጋነሽ ኃይሉ ኤርትራዊት ለሆነችው 4ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ኤልሳቤት ተስፋጽዮን እንድታስረክብ በማለት የፌዴሬሽን ም/ቤት የወሰነውን ውሳኔ ድጋሚ ለምክር ቤቱ እንዳይቀርብ ለማድረግ በአካልና በስልክ በመገናኘትና በመደራደር፣ የዐቃቤ ህግ 1ኛ ምስክር ብር 400 ሚሊየን የሚገመት ቤትን እንዲያጡ አድርገዋል፡፡

በዚህም በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።

በሁተለኛ ክስ በተመሳሳይ1ኛ፣ 2ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ከላይ በዝርዝር በተገለጸው የወንጀል ድርጊታቸው በህገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ በአብላጫው ድምጽ ትርጉም አያስፈልገውም በማለት በመወሰኑ በውሳኔው ቅር በመሰኘት የህገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥልኝ ሲሉ ሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጣቸው ለፌዴሬሽን ም/ቤት የዕግድ እና የይግባኝ አቤቱታ በም/ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ውሳኔው እንዳይቀየር በማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት እና የግል ተበዳዮችን ይዞታ በማሳጣት ከፍተኛ የገንዘብ ጉዳት በማድረሳቸው 1ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በመንግሥት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ብቻ በሚፈጸም የሙስና ወንጀል ውስጥ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆኑት 2ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የከባድ የስልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሶስተኛ ክስ በ1ኛ እና 7ኛተከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ በተጨማሪነት ለራሱም የማይገባውን 200 ሺህ ብር በማግኘቱ 1ኛ ተከሳሽ በመንግሥት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ብቻ በሚፈጸም የሙስና ወንጀል ውስጥ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆነው 7ኛ ተከሳሽ ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በከባድ ስልጣንን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

ተከሳሾች ዛሬ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዋለዉ ችሎት 1ኛ ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ4 ወር ጽኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ 2ኛ ተከሳሽ 2 ዓመት ከ8 ወር እና 5 ሺህ ብር፣ 3ኛ ተከሳሽ በቂ ማስረጃ ስላልተገኘበት በነጻ፣ 4ኛ ተከሳሽ 4 ዓመት ከ6 ወር፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሽ 2 ዓመት ከ8 ወር እና 1 ሺህ ብር እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ 7 ዓመት ከ6 ወር እና 10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል።

FBC


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: