እናታችን ቅድስት ኪዳነ ምህረት ከክፉ ነገር ትከልለን፤ የልባችንን መልካም መሻትም ትሙላልን

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

መንገስተ ሰማያት መግቢያ ኪዳን

አባቶቻችን የሃዘን ብዛት የእንባ ጎርፍ አይን ያጠፋል፣ ፊት ያንጣጣል፣ ልብ ይሰውራል አካልንም ያዝላል ይላሉ፡፡ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በጌታችን ምክንያት ያገኛት ሃዘን እጅግ መራራ ነው፡፡ በምድረ ግብጽ በስደቷ ያፈሰሰችው እንባ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ጌታችን ከተያዘበት ከምሴተ ሐሙስ ጀምሮ በግርፋቱ፣ በስቅለቱና በሞቱ እስከ ትንሣኤው ድረስ አልቅሳለች፡፡ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላም በጎልጎታ በልጇ መቃብር ላይ ሆና ከእርሱ ከተወዳጅ ልጇ ስለኛ ስለሰው ልጆች ፍጹም ልመና አቅርበለች፡፡ “ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ፣ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመኾንህ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማኅፀኔ፣ ከአንተ ጋር ከሀገር ወደ ሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡” በማለት ጸልያለች፡፡

ጌታችንም እልፍ አእላፍ መላእክት ጋር መጥቶ “እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይኹን! እንዳደርግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?” አላት፡፡ እመቤታችንም በስሟ የሚማጸኑትንና መታሰቢያዋን የሚያደርጉትን፣ ለችግረኛ የሚራሩትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትን፤ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን፤ ለእርሷና ለሃይማኖታቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ልጆቻቸውን በስሟ የሚሰይሙትን ሁሉ እንዲምርላትና ከሞተ ነፍስ እንዲያድንላት ጠየቀችው፡፡ ጌታችንም “ይህን ሁሉ እንዳደርግልሽ በራሴ፣ በአባቴና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ” ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ በመዝሙር 88÷3 “ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” ተብሎ እንደተጻፈ፣ ማደሪያው ትሆን ዘንድ ከመረጣት ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፡፡

ይህም ታላቅ በዓል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እየተባለ በየዓመቱ የካቲት 16 ቀን ይከበራል፡፡ ይህ ዕለት ድንቅ ተአምራትም ያደረገችበት ነው፡፡ ስምዖን የሚባል የአባታችን የቅዱስ አብርሃምን ታሪክ የሰማና እንደ እርሱ እንግዳ መቀበል የሚወድ ሰው ነበር፡፡ ጠላታችን ሰይጣንም እንግዳ መስሎ ወደ ቤቱ በመምጣት ልጅህን አርደህ አብላኝ አለው፡፡ እርሱም “አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለው” በሚል እሳቤ ያለውን አደረገ፡፡ ሲያቀርብለትም ቅመስልኝ አለው፤ እሺ ብሎ ሲቀምስለት በዚያው ተዋሐደው፡፡ ከዚህ በኋላ በላኤ ከቤተሰቦቹ ጀምሮ “በላዔ ሰብእ” ወይም “ሰው በላው” እስኪባል ድረስ 78 ሰዎችን ከበላ በኋላ አንድ የቆሰለ ነዳይ አይቶ ሊበላው ሲቀርብ ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፡፡

ነዳዩ ግን ውሃ አጠጣኝ ሲል በሥላሴ፣ በቅዱሳን ሁሉ ስም ቢለምነው፤ አልሰማውም፡፡ በድንግል ማርያም ስም ሲለው በአእመሮው አቃጨለበትና “ምህረት እንደምታሰጥ በልጅነቴ ሰምቻለሁ” ብሎ ከያዘው ውሃ ጥቂት አጠጣው፡፡ በሌላ ቦታም አንድ ገበሬ አጊኝቶ ሊበላው ሲል “አንተ ያ በላዔ የምትባል ነህ?” አለው፡፡ ለካ ይህ ነገር ተሰምቶብኛል ብሎ ወደ አንድ ዋሻ ሔዶ በጸጸት ሞቷል፡፡ የጨለማ መላዕክት ነፍሱን በጌታ ፊት ሲያቀርቧትም እመቤታችን “ልጄ በማይታበል ቃልህ ይህችን ነፍስ ማርልኝ” አለችው፡፡ ጌታችንም ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋና ፈጣሪውን የካደ እንዴት ይማራል አላት፤ እመቤታችንም በስሜ የተጠማውን አጠጥቷል ስትል ነፍሱን አስምራዋለች፡፡ እኛንም በቃል ኪዳኗ ታስምረን፣ አማላጅነቷም አይለየን፡፡ አሜን!!!

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: