በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዘመናት ባልቀየሩት ድንቅ ተፈጥሮና ጥንታዊ ማንነት ውስጥ የሚኖር ታላቅና ኩሩ ህዝብ አለ

- Advertisement -
Sidebar AD

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዘመናት ባልቀየሩት ድንቅ ተፈጥሮና ጥንታዊ ማንነት ውስጥ የሚኖር ታላቅና ኩሩ ህዝብ አለ።

እነርሱ የሱሪ ህዝቦች ናቸው! እነርሱ የተፈጥሮ እውነተኛ ጠባቂዎች፣ የጀግንነት መፍለቂያዎችና የጥንታዊ ባህል ህያው ምስክሮች ናቸው።

ምድራቸው በለምለም ኮረብታዎች፣ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች፣ ሰፋፊ ሳር ምድሮችና ውድ ማዕድናት የተከበበች እውነተኛ ገነት ናት።

የሱሪ ህዝብ ማህበራዊ መሰረት በሶስት ታላላቅ ጎሳዎች ላይ የተገነባ ነው። እያንዳንዱ ጎሳ የራሱ የሆነ ታሪካዊ የአመራር መዋቅር ያለው ሲሆን፥ ዛሬም ድረስ በአባቶች ጥበብና ስርአት ይመራል።

ከነዚያ ውስጥም የቻይ ጎሳ የሚባሉት ናቸው። ቻይ በታሪካቸው ዶሎቴ ኤከዲ እና ሃላጋሜሪ የተባሉ ሶስት ታላላቅ መሪዎች ያሏቸው ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ጎሳውን በቁርጠኝነትና በጥበብ እየመራ ያለው ግንባር ቀደሙ መሪያቸው ዶሎቴ ነው።

የቲርማጋ ጎሳ (Tirmaga): በአምስት ዝነኛ መሪዎች (ቦሎጊዳንጊ ፣ ኦሌዞጊ ፣ ኦሌሲርዋ ፣ ቤባላ እና ኦሊኛሜሪ) የሚታወቁ ሲሆን፥ በአሁኑ ሰዓት የህዝቡ ዋና አለኝታና መሪ ቦሎጊዳንጊ ነው።

የባሌ ጎሳ (Ba’ale): ልክ እንደ ቲርማጋ አምስት ታዋቂ መሪዎች (ዳላላ ፣ ሚሮሊንጎ ፣ ማሆሊ፣ ሲሪያሊ እና ዎሲ) ያሏቸው ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ ህዝባቸውን በጋራና በትብብር እየመሩ ያሉት ዳላላ እና ሚሮሊንጎ ናቸው።

በአሁኑ ሰዓት መላውን የሱሪ ህዝብ በአንድነት፣ በሰላምና በባህላዊ ስርአት እየመሩ ያሉ 4 ታላላቅ መሪዎች አሉ። እነርሱም፦ ዶሎቴ (ለቻይ) ፣ ቦሎጊዳንጊ (ለቲርማጋ) ፣ ዳላላ እና ሚሮሊንጎ (ለባሌ) ናቸው።

የእነርሱ ህይወት ከተፈጥሮ መሬታቸው ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። የሚተዳደሩበት የምጣኔ ሀብት ዘይቤ ሶስት ዋና ምሰሶዎች አሉት።

በአብዛኛው ከብት አርቢ (Pastoralist) ማህበረሰብ ናቸው። ከብት ለእነርሱ ተራ እንስሳ አይደለም፤ የሀብት መለኪያ፣ የማህበራዊ ክብር መግለጫ፣ የጋብቻ ትስስር ማጠንጠኛና የህልውናቸው ትልቁ ምሰሶ ፣ ስያሜም (መጠሪያም ጭምር ነው።

ከከብት እርባታው ጎን ለጎን፣ ለም ምድራቸውን በጥረት የሚያርሱ ድንቅ ገበሬዎች አሏቸው። ስነ-ምህዳሩን በጠበቀ መልኩ ማሽላ፣ በቆሎ እና የተለያዩ ሰብሎችን በስፋት ያመርታሉ።

ከእርሻና ከከብት እርባታው ባሻገር፣ የሱሪ ምድር በወርቅ ማዕድን የበለፀገች ናት። የሱሪ ወጣቶችና ማህበረሰቡ በየወንዞቻቸውና በባህላዊ ማዕድን ቦታዎች (እንደ ባሻጊ ፣ ሞጋ ፣ናሜሪ ማዕድን ያሉ) በመሄድ ወርቅ በባህላዊ መንገድ የማውጣትና የማጠብ (Gold Panning) አስደናቂ የስራ ባህል አላቸው። ይህ ማዕድን ለቤተሰቦቻቸው ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን የኑሮ መሠረት ይሆናል።

የሱሪ ምድር በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ማራኪና ያልተነኩ (Unexplored) የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም ተመራጭ ከሆኖ 7 መዳረሻዎች አንዱ ነው።

እምቅ የቱሪዝም ሀብቶቻቸው አሏቸው የሱሪ ህዝብ ከፍታና ዝቅታ ያላቸው አረንጓዴ ኮረብታዎች፣ ታላላቅ ወንዞችና የዱር እንስሳት መሸሸጊያ የሆኑ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ሰላማዊ ድባብን ይፈጥራሉ።

ንጹህ አየርና አስደናቂ የተፈጥሮ እይታን ለሚፈልግ ተጓዥ ተመራጭ ስፍራ ነው።

የሱሪ ወጣቶች የወንድነት መገለጫ የሆነው የዶንጋ (Donga) የበትር ፍልሚያ አላቸው። ወጣቶቻቸው ጀግንነታቸውን፣ ጥንካሬያቸውንና ብቃታቸውን የሚያሳዩበት ታላቅ ባህላዊ የበትር ጨዋታ ነው። ይህ ጨዋታ ስነ-ስርአትንና የሱሪን ወንድነት መገለጫ የሚያሳይ በመሆኑ በየዓመቱ የበርካታ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል።

ሌላኛው የሴቶቻቸው የከንፈር ሸክላ (Lip plates) የውበትና የብስለት መገለጫ ሲሆን፥ በሰውነት ላይ የሚሳሉ ውብ የተፈጥሮ ቀለሞች (Body painting) እና ባህላዊ ንቅሳቶች የእነርሱን ጥልቅ የጥበብ ስሜት ያሳያሉ።

የሱሪ ህዝቦች የትናንት ታሪካቸውን ሳናጣ፣ የዛሬውን የአመራር ጥበባቸውን ጠብቀው፣ ከተፈጥሮና ከምድራቸው ወርቃማ ፀጋ ጋር በሰላም የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ምድራቸው የባህል ሙዚየም፣ የመልክዓ-ምድር ውበት ማሳያና የኢትዮጵያ ድንቅ ቀለም ናት። ይህንን እውነተኛና ያልተበረዘ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ ሀብት ለማየት፣ ለመማርና ለመደመም ሁል ጊዜም በደስታ ይቀበሏችኋል!

ኢትዮጵያ በባህልና በተፈጥሮ የታደለች ውብ ሀገር ናት! የሱሪ ህዝቦች ደግሞ የዚህ ውበት ደማቅ ምስክሮች ናቸው!

(በሙባረክ አበበ)
ሚዛን ሚዲያና ኮሙኒኬሽን






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: