በተተኮሠበት ጥይት ተመቶ ህይወቱ ባለፈው የቀድሞ አትሌት ይሄይስ ታደለው ዙሪያ የተጠናከረ ልዩ ዘገባ

- Advertisement -
Sidebar AD

♦️

♦️በአትሌቶች መካከል ያለውን የአጉል ባህልና ዕምነት፣የመጠራጠርና የመጠፋፋት ባህል እንደወረርሽኝ ተዛምቶ ለተጨማሪ አደጋ ከመጋለጣችን በፊት ይታሰብበት

♦️የሟችና በገዳይነት የተጠረጠረው አትሌት ማንነት

#Ethiopia | በሚያሳዝን ሁኔታ ሁለቱም የነገ ውጤታማ አትሌቶች ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች ነበሩ፤ጉዳዩ በህግ የተያዘ በመሆኑና በማስረጃ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት በገዳይነት ተጠርጥሮ በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኘው አትሌት ደረሠ ረታ ከደብረብርሃን የተገኘ በመቀጠል በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አሁን በመጨረሻ ደግሞ ለፌዴራል ፖሊስ የሚሮጥ አትሌት ሲሆን በጣም ትልቅ ተስፋ የተጣለበት አትሌት እንደነበረም ነው ለአትሌቱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች የሚናገሩት።እንደ እነዚሁ ምንጮቻችን አገላለፅ አትሌቱ ከአንድ ዓመት በፊት በጉያንግ በተካሄደው ውድድር 2:12:00 በሆነ ሠዓት በመግባት የተሻለ ሠዓትና ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን የቅርብ ምርጥ ሠዓቱም 2:13:00 እንደሆነ ነው የሚሠማው።

በተተኮሠበት ጥይት ህይወቱ ያለፈው አትሌት ይሄይስ ታደለው በበኩሉ ከአማራ ክልል (ሠሜን ሸዋ)የተገኘ አትሌት ሲሆን በጉዳት ምክንያት ከውድድር ርቆ ባለቤቱን አትሌት ወርቅነሽ ዓለሙን እንደ አሠልጣኝ ሆኖ ከማሠራት ውጪ በአሁን ሠዓት በአትሌትነት እየሮጠ አይደለም።

♦️እስከመገዳደል ያደረሳቸው ምን ይሆን?

ሁለቱን ከአንድ ክልል የመጡ አትሌቶችን እስከመገዳደል ያበቃቸውን ትክክለኛውን ከእነሱና ከፈጣሪ ውጪ የሚያውቅ ሠው ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፤ነገር በመካከላቸው ለገላጋይ ያስቸገረ አለመግባባት እኔዳላቸው ቀአሠልጣኝቻቸውና በቤተሠብቻቸው እኔዲሁም አትሌት በሆኑት ሚስቶቻቸው ጭምር ይታወቃል።የፀባቸውን መነሻ በትክክል መግለፅ ባይቻልም ከአጉልጰባህል ወይም አምልኮ ጋር ተያይዞ ባለቤቴና እኔ ላይ ይሄን አስደርገሃል የሚለው ዋነኛው የግጭታቸውና እስከመገዳደል ያደረሠ ችግር እንደሆነ በዙሪያ ያሉ ሠዎች ይናገራሉ፤ይህ ከድሮም ጀምሮ በአትሌቶች ዙሪያ የሚሠማው አጉል ባህል ወይም የአምልኮ ነገር ዛሬ ወደ አዲሶቹ ትውልዶችም ተሸጋግሮ አብሮ ልምምድ ያለመስራት፣አብሮ በህቴል እኔደጓደኛ አትሌት ክፍል ያለመጋራት፣አብሮ ያለመብላትና አብሮ በአንድ አውሮፕላን አልሄድም እስከማለት አስፈሪ ውሳኔ ላይ ተደርሶ የቡድን ስሜት ከአትሌቲክሱ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል።

♦️ለሽማግሌና ለአስታራቂዎች ያስቸገሩት ሟችና ገዳይ

በሁለቱ አትሌትች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ያልመጣ አስታራቂ ሽማግሌ፣የሁለቱም አሠልጣኞች ፍቅሩና ኢማና መርጊያን ጨምሮ፣የቅርብ ጓደኛ በመጨረሻም ቤተሠብች የሁለቱንም አለመግባባት ለመፍታት ዳገት ቢወጡ ቁልቁል ቢወርዱ ሊሳካ አልቻለም፤አሠልጣኞችም ነገሩ ከብዷቸው ሁለቱም ሴት አትሌቶች በተለያየ አሠልጣኝ የተለያየ ቦታ እንዲሠሩ እሰከማድረግ ደርሠዋል፤በውስጥ የተቋጠረው ቂም በሽማግሌም፣በገላጋይ አልፈታም ብሎ በመጨረሻም ድምዳሜው የአንደኛው ህይወት በአንደኛው እጅ መጥፋት ሆኗል።

♦️የአትሌቱ ህይወት ስላለፈበት አጋጣሚ

ገዳይ እንዴትና የት፣በምን ሁኔታ የሟችን ህይወት ነጠቀ የሚለው ብዙዎች ለማወቅና እርግጠኛ መሆን የሚፈልጉበት ጥያቄ ነው፤በገዳይነት የተጠረጠረው አትሌት ደረሠ ረታ በውስጡ በተፈጠረ አንዳች ስሜት ተነሳስቶ ወደ ሠንዳፋ የልምምድ ቦታ ድንገት አመራ፤በዛች ቀን የተደገሠለትን ድግስና ከሞት ጋር ቀጠሮ እንዳለው ለሠከንድም ቢሆን ያላሠበው የቀድሞ አትሌት ይሄይስ ታደለው ባለቤቱን አትሌት ወርቅነሽ ዓለሙን ከፊት ሆኖ እያሠራ እያለ በድንገት በተተኮሠበት ጥይት ይህቺን ዓለም ዳግም ላይመለስባት ለዘለዓለሙ አሸልቧል።በገዳይነት የተጠረጠረው ከፊቱ በርካታ የአትሌቲክስ የስኬት ዓመታት እንዳሉት የሚነገርለት በግድያ የተጠረጠረው አትሌት ደረሠ ረታ ከግድያው በኋላ ራሱን ለማሸሽ ጥረት ቢያደርግም በአካባቢው በነበሩ አርሶ አደሮች ጥረት ተይዞ አሁን ሠንዳፋ በሚገኘው ማረሚያ ቤት በህግ ጥላ ስር ውሎ ጉዳዩን እየተከታተለ ይገኛል።

♦️”በጣም ተፈታተነኝ፣በጣም ታገለኝ”የሚል አጭር ቃል የተነፈሠው ገዳይ

በግድያ ተጠርጥሮ በህግ ጥላ ስር የሚገኘው አትሌት ደረሠ ረታ ከግድያው በኋላ በተለይ ዛሬ ከሟች አትሌት ይሄይስ ታደለው የቀብር ስነ-ስርዓቱ ከተፈፀመ በኋላ የቅርብ ወዳጆቹ ለምን እንደዚህ አይነት ውሳኔ እንደወሠነ ጠይቀውት ከገጠመው ያልታሠበ ፈተና ውስጥ የወደቀው አትሌቱ በፀፀት ውስጥ ሆኖ “በጣም ተፈታተነኝ፣በጣም ታገለኝ”የሚል አጭር ቃል ከመናገር የዘለለ መተንፈስ እንዳልቻለ ለሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል ገልፀዋል።

♦️የአትሌት ይሄይስ ታደለው የመጨረሻ ስንብት

የአትሌት ይሄይስ ታደለው የቀብር ስነ-ስርዓቱና የአስከሬን ሽኝት ዛሬ ከቀኑ በ6:00 በሚኖሩበት ሠንዳፋ በኬ ማርያም ቤተክርስቲያን የአትሌቱ ቤተሠቦች፣ጓደኞች፣አሠልጣኞች፣አትሌቶችና የስፖርት ቤተሠቦች በተገኙበት በክብር አርፏል።በጉዳት ምክንያት ከአትሌቲክስ ርቆ ባለቤቱን በማሠራት የሚያሳልፈው አትሌት ይሄይስ ታደለው እንደዋዛ ይህቺን ዓለምና አትሌቲክሱንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሠናብቷል።

♦️ለኢት.አ.ፌዴሬሽንና ለአትዮጵያ አትሌቶች ማህበር መልዕክት

የኢት.አ.ፌዴሬሽንና የአትዮጵያ አትሌቶች ማህበር እስከአሁን በአሳዛኙ ክስተት ዙሪያ የተነፈሱት ነገር አለመኖሩ ትዝብትን ፈጥሯል፤እንደ ሀገርም እንደ አትሌቲክሱ ዓለምም ትልቅ ስብራትና ልብ ሠባሪ አጋጣሚ ነው፤ሁለቱም አካላት በአትሌቶቹ መካከል የተፈጠረውን ግድያ ወደ ሌሎች እንዳይዛመትና በዚሁ እንዲያበቃ በይፋ በመግለጫ ጭምር ማውገዝና ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ምክንያቶች የጠፋውን ውዱን የሠው ልጅ ህይወት መለስ ብሎ ላስታወሠ በጎረቤት ኬንያ በጥይት አረር ህይወታቸው የተነጠቁ አትሌቶች፣አሠልጣኞችና የአትሌቶች ህይወት እንደዋዛ መነጠቁን በትዝታ ፈረስ ወደኋላ ሄዶ ላስታወሠ ጉዳዩ ቢያሳስበው አይፈረድበትም፤ይሄ በአትሌቶች መካከል ያለውን የአጉል ባህልና ዕምነት፣የመጠራጠርና የመጠፋፋት ባህል እንደወረርሽኝ ተዛምቶ ለተጨማሪ አደጋ ከመጋለጣችን በአሠልጣኞችና በአትሌቶች አእምሮ ላይ ስራ ይሠራ።

👉የሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል ዝግጅት ክፍል ለሟች ዘላለማዊ እረፍትን፤ ለቤተሰቦቹ፣ለጓደኞቹ፣ለወዳጅ ዘመዶቹና ለስፖርት ቤተሰቦች በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን።

👉ፎቶ ክሬዲት:ስፖርት ኮርነር ኢትዮጵያ

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1