በአርሲ በንጹሐን ላይ ለተፈጸመው ጥቃት መንግሥት ሸኔን ተጠያቂ አደረገ

- Advertisement -
Sidebar AD

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ኀዘን የገለጹ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው የተቀናጀ ርምጃ እየወሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አፈጻጸም እና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ሥጋቶችን አስመልክቶ ሰፊ መግለጫ ሰጥቷል።

መንግሥት በምርጫው ወቅት ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰፊ ተግዳሮት እንደገጠመውና ድርጊቶቹን ማክሸፉን አስታውቋል።

በመግለጫው መሠረት በምርጫው ላይ ለመሳተፍ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከ52,000 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል አብዛኛዎቹ ያለምንም ዕንቅፋት አገልግሎት ሰጥተዋል። በምርጫው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎችና በርካታ የግል ዕጩዎች ተሳትፈዋል።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ የሚመሩት የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች ሂደቱ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍን የተከተለ መሆኑን በጊዜያዊ ሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ምርጫውን «ውጤቱ አስቀድሞ የተወሰነ» ሲሉ የሰነዘሩትን ትችት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበለውና ከተጨባጩ እውነታ የራቀ መሆኑን ገልጿል።

መንግሥት በሰጠው መግለጫ ምርጫውን ለማስተጓጎልና በሀገሪቱ አለመረጋጋት ለመፍጠር በተለያዩ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት አድርገዋል ሲል ከሷል።

መንግሥት «የኦነግ ሸኔ» (የኦሮሞ ነፃነት ጦር) ሲል በሚጠራው ታጣቂ ቡድን በአርሲ ዞን ንጹሐን ዜጎችና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙንና በዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ኀዘን የገለጹ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው የተቀናጀ ርምጃ እየወሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመግለጫው ላይ መንግሥት «የፋኖ ታጣቂ ቡድን» ሲል የገለፃቸውን የክልሉን ታጣቂዎች በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃንና ወልድያ ከተሞች የሽብር እንቅስቃሴ ለማድረግ አቅደው ነበር ሲል ወንጅሏል።

በተጨማሪም እነዚህ ኃይሎች በኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችና ከውጭ አካላት ጋር የጋራ ቁርኝት (ፅምዶ) በመፍጠር በአዲስ አበባ የኅቡዕ ሴሎችን በማደራጀትና መንገዶችን በመዝጋት ምርጫውን ለማደናቀፍ ቢንቀሳቀሱም በጸጥታ ኃይሉ ጥረት ዕቅዳቸውን አክሽፊያለሁ ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማጠቃለያው ማንኛውም የፖለቲካ ቅሬታ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በብሔራዊ ምክክር ሂደቱና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት አማካኝነት ብቻ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት ሲል በመግለጫው ገልፆል

በሌላ በኩል መንግሥት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በ2017 በጀት ዓመት 9.2 በመቶ መድረሱንና በ2018 ደግሞ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመትና የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ አሐዝ እየተቃረበ መሆኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ፣ የጎዴ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ፣ የሞጆ የሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ እና የቦረና ቀጠና የመስኖና የአውሮፕላን ማረፊያ መሠረተ ልማቶች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስኬቶች መሆናቸውን በመግለጫው በስፋት ተብራርቷል።





Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: