የቀድሞው የናይጄሪያ አቪዬሽን ሚኒስትር የኢትዮጵያ አየር መንገድን አውሮፕላን ለ3 ቀናት ብቻ ተከራይተው የውሸት ምረቃ ማድረጋቸ

- Advertisement -
Sidebar AD

የቀድሞው የናይጄሪያ አቪዬሽን ሚኒስትር የኢትዮጵያ አየር መንገድን አውሮፕላን ለ3 ቀናት ብቻ ተከራይተው የውሸት ምረቃ ማድረጋቸው ተጋለጠ

የናይጄሪያ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ወንጀሎች ኮሚሽን (EFCC) ባደረገው ከፍተኛ ምርመራ፣ የቀድሞው የአቪዬሽን ሚኒስትር ሀዲ አቡበከር ሲሪካ “ናይጄሪያ ኤር” የተባለውን አዲስ ብሔራዊ አየር መንገድ ስራ እንደጀመረ ለማስመሰል የፈጸሙት መጠነ-ሰፊ ማጭበርበር ፍርድ ቤት ላይ ይፋ ሆነ።

ሚኒስትሩ አየር መንገዱ መቋቋሙን ለሕዝብ ለማሳየት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የ3 ቀናት ብቻ የኪራይ ስምምነት ማድረጋቸውን የኮሚሽኑ መርማሪዎች ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።

በአጠቃላይ 20 ቢሊዮን ናይራ የሚገመት የዕምነት ማጉደል እና የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት ሚኒስትሩ፣ አውሮፕላኑ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ስልጣን በለቀቁበት ዕለት (ግንቦት 29 ቀን 2023) ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ አስቀድመው ውል አዘጋጅተው ነበር።

አውሮፕላኑ አቡጃ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰበት ወቅትም፣ የናይጄሪያ ኤርን የደንብ ልብስ የለበሱ የሀገር ውስጥ ሞዴሎች በገንዘብ ተከፍሏቸው የውሸት የማስተዋወቂያ ፎቶዎች እንዲነሱ መደረጉን መርማሪው በምስክርነታቸው ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎ የቀድሞው ሚኒስትር ሀዲ ሲሪካ፣ ልጃቸው፣ አማቻቸው እና “አል ቡራቅ ግሎባል ኢንቨስትመንት” የተባለ ኩባንያ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ተከሳሾቹ የስልጣን አለአግባብ መገልገያ እና ከ2 ቢሊዮን ናይራ በላይ የህዝብ ሀብት ማባከንን ጨምሮ ስድስት የወንጀል ክሶች ቀርበውባቸዋል።

በተጨማሪም ምርመራው እንደሚያሳየው፣ መጀመሪያ ላይ የናይጄሪያ ኤርን ለማቋቋም “ቲያናኤሮ ናይጄሪያ ሊሚትድ” ለተባለ ኩባንያ ተሰጥቶ የነበረው የ299 ሚሊዮን ናይሪያ ውል፣ በሚኒስትሩ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ወደ 599 ሚሊዮን ናይራ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ይህ የሙስና ሰንሰለት ሊደረስበት የቻለው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቋሚ ጸሐፊ የነበሩትን ግለሰብ ስልክ በመፈተሽ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ በወቅቱ በስፔን ሆነው ውሉ ለተጠቀሰው ኩባንያ እንዲሰጥ ያስተላለፉት የድምፅ መልዕክት በማስረጃነት ተገኝቷል።
ክሱ በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: