#Ethiopia | የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ መስመር ርቀው የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን በፀሐይ ኃይል (ሶላር) አማራጭ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በተለይ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች አዲስ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ያለምንም ክፍያ በነፃ ማስገባት የሚችሉበትን ታላቅ ዕድል ይዞ ብቅ ብሏል።
ይህ የተገለፀው በሲዳማ ክልል ምስራቃዊ ዞን ሆኮ ወረዳ ሆዲ ቦኩ ከተማ ላይ በዛሬው ዕለት በተመረቀው የሆዲ ቦኩ የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ወቅት ነው፡፡
ከአለም ባንክ በተገኘ 227 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ብድር ድጋፍ የተገነባው ይህ የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፤ 525 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ዓቅም ያለው ነው፡፡
ፕሮጀክቱ የማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ሲሆን፤ አገልግሎቱ ባመቻቸው የነፃ ቆጣሪ ዕድል በአሁኑ ወቅት 487 አባወራዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ 1.2 ኪ.ሜ መካከለኛ እና 10.5 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር የተዘረጋ ሲሆን፤ ሶስት ትራንስፎርመሮች ተተክለው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆዲ ቦኩ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተገነባባቸው አካባቢ የሚገኙ አዲስ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ካሁን በኃላ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በነፃ መጠቀም የሚችሉበትን አሰራር ፈጥሯል፡፡
አገልግሎቱ ይህንን ምቹ ሁኔታ የፈጠረው የኢኮኖሚ አቅም ሳይገድበው እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል የንጹህ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆንና ወደ ተሻለ ዘመናዊ ሕይወት እንዲሸጋገር ለማስቻል ነው።
ይህ አዲስ አቅጣጫ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅማቸው ሳይገድባቸው የንጹህ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
አገልግሎቱ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት ለማረጋገጥ የወሰደው ይህ እርምጃ፣ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ከዘመናዊ አኗኗር ወደኋላ የሚቀር ማህበረሰብ እንዳይኖር ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት፣ የሶላር የኃይል አቅርቦት በተገነባላቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ይህንን የተዘጋጀውን ነፃ ዕድል ከዛሬ ጀምሮ መጠቀም እንደሚችሉ ተበስሯል።
ባለፉት ዓመታት ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችን ከፀሀይ ሀይል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነ ስራ የሆዲ ቦኩ ማመንጫን ጨምሮ 43 የፀሀይል ሀይል ማመንጫዎችን በመላ ሀገሪቱ በመገንባት ከ10 ሺህ በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አገልግሎቱ የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ችግር ለመፍታት ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) ደንበኞች ቆጣሪ በረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጭ እንዲያገኙ ማመቻቸቱ የሚታወስ ነው፡፡



Source: GetuTemesgen







No comments yet.