ከወንበር በላይ ሀገር !

- Advertisement -
Sidebar AD

የምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት ይፋ ውጤት የሀገሪቱን የፖለቲካ ካርታ ግልጽ አድርጎታል። ገዥው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫውን ወንበር ወስዷል፤ ሀገራችንም ወደ ሌላ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ተሻግራለች።

ኢዜማ የለፋውን እና የደከመበትን ያህል ባይሆንም 86 ወንበሮችን አሸንፏል (13ቱ በፌደራል ፓርላማ፣ 73ቱ በክልል ምክር ቤቶች) በዚህ ውጤቱ ኢዜማ በፓርላማው ውስጥ ዋነኛው ተፎካካሪና አማራጭ ድምፅ ሆኖ ወጥቷል። ለመሆኑ ይህ ውጤት የለፋንለትና የተመኘነው ያህል ነው? ፈጽሞ አይደለም። ታዲያ በቀላሉ የምናጣጥለው እና ፋይዳቢስ የሚባልስ ነው? በፍጹም!

ፖለቲካ እንደ ሎተሪ ዕጣ በአንድ ጀምበር ሁሉንም እድል ጠራርጎ የሚወሰድበት ወይንም በተቃራኒው ሁሉንም ተበልቶ በባዶ እጅ እየቆዘሙ አንገት ደፍቶ ወደቤት የሚኬድበት የዕድል ጨዋታ አይደለም። ለኢዜማ 86 ወንበሮች በማሸነፍ፣ ጠንካራ መዋቅርን ለመሥራት እና ቀጣዩ ምርጫ እስኪደርስ መላውን አባላት በንቃት የሚያሳትፍ በርካታ የቤት ሥራ ይዞ መውጣትም በፖለቲካ ዐይን ተጨማሪ የዴሞክራሲ እርምጃ ነው።

ከእኛ ጋር ተፎካካሪ የነበሩ፤ የሕዝብ አመኔታ እና ድምጽ ሲያጡ እና እንዳለሙት ውጤት ሳይቀናቸው ሲቀር፣ የሌላውን ድካምና ውጤት ለማጣጣል እና ስም ለመለጠፍ የሚሮጡትን “አንዳንድ የተቃውሞ ነዋሪዎች” ስናይ… “ያጣ ለማኝ ተሳድቦ ይሄዳል” ከሚለው ነባር የሀገራችን ብሂል የተሻለ ምን ማስተማሪያ ሊገኝላቸው ይችላል?

ሌሎች ደግሞ አሉ። ዓላማቸው ከዓላማችን፤ መንገዳቸውም ከመንገዳችን ስላልገጠመ ብቻ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥደው ሲረግሙን ውለው ሲረግሙን በማደራቸው ፖለቲካ የተነተኑ የሚመስላቸው የቁራ ጯሂዎች! የተለመደው ቁርጥ ያለ መልሳቸን “ያዋጣል በምትሉት መንገድ ሂዱ! የእኛን መንገድ ለእኛ ተዉልን” የሚል ይሆናል። ዳር ቆመው ሰባራ ሳንቲም ሳያዋጡ ተዓምር ለሚናፍቁ የሰነፍ ቅምጥሎችና ‘የሶሻል ሚዲያ አርበኞች’ መልካም የምኞት ጊዜ ይሁንላቸው ከማለት ውጪስ ምን ይባላል?

እኛ ኢዜማውያን ግን ዲሞክራሲ የሚገነባው እጅጌን ሰብስቦ እና ቆፍጠን ብሎ መሬት ላይ ሥራ በመሥራት መሆኑን ስለምናምን ከባለፈው የምርጫ ተሳትፎአችን በብዙ እጥፍ የጨመረውን ውጤት በጸጋ ተቀብለን እና የሕዝብ ድምጽ አክብረን በጨዋነት እና በስለጠነ ዘመናዊ ፖለቲካ ተሳትፎ ወደፊት እንራመዳለን። በውድድር ውስጥ ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን፣ ተሸንፎም ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ማየት መቻል የፖለቲካ ብስለት መለኪያ ነውና።

አሁን የምርጫው አጀንዳ ከሞላ ጎደል ተጠናቅቋል፤ አሸናፊዎች ወደየምክር ቤቶቻቸው፤ የተቀረነውም ወደየ እለታዊ ተግባራችን እንመለሳለን። ሀገርን ማገልገል በምክር ቤቶች ተሳትፎ ብቻ አይወሰንም። የሀገር ግንባታ በምርምር ማዕከላት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሙያ ማኅበራት፤ በሲቪክ መድረኮች፣ በልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ከገልግሎቶች ውስጥ ይቀጥላል።

… እንዲያውም ሁሉም ሰው በድንገት የሕገ-መንግስት ተንታኝ፣ የጂኦፖለቲካው ነብይ፣ የፌደራሊዝም ሐዋርያ በሚሆንበት በዚያ ድራማዊ የቡና ጠረጴዛ ውይይት ውስጥ ጭምር ሕይወት እንደወትሮው ይቀጥላል።

እስካሁን የተጓዝንበትን ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅም የፖለቲካ ተሳትፎን በኩራት እያከበርን፤ አሁን ደግሞ የፓርቲ ማሊያችንን አውልቀን፣ የሙያ ጃኬታችንን ለብሰን ወደ ዋናው ሥራችን ብንመለስ ምን ይለናል? የሽሚዞቻችን እጅጌ ስብስበን “ዳዬ ወደሥራ!” ብለናል።

እግረመንገድም ከአድካሚው እና እንደ ልቅሶ ቤት አግዳሚ ወንበር ከሊቅ እስከ ደቂቅ አኩል ተኮልኩሎ ከፊሉ ሲራገም ከፊሉ ሲመርቅ ከሚውልበት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክም እስከውዲያኛውም ባይሆንም እረፍት መውጣት ተገቢ አይደለም ትላላቸሁ?

መልክም ጊዜ !

(አርኪቴክት ዮሐንስ መኮንን የኢዜማ ከፍተኛ አመራር)

#ኢትዮጵያ
#ኢዜማ
#ሀገርግንባታ
#ምርጫ2018
#ዲሞክራሲ


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: