የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የ2018 ዓ.ም. ኮከብ ተማሪ
#Ethiopia | ¿እንጅባራ – በዛሬው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት 2,900 ተማሪዎች ከተመረቁበት ውስጥ፣ በልዩ የትምህርት ውጤቱ ትኩረት የሳበው ተማሪ አላምረው ዋጋው የዓመቱ ኮከብ ተማሪ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት የተሰማራው አላምረው፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከወሰዳቸው 55 ኮርሶች መካከል 46ቱን ‘A+’ እንዲሁም 9ኙን ‘A’ በማምጣት ሙሉ 4.00 ውጤት (CGPA) ማስመዝገብ ችሏል።
ይህ አስደናቂ ውጤት ተማሪውን በከፍተኛ ማዕረግ እንዲመረቅ ከማስቻሉም በላይ፣ የ2018 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲው ኮከብ ተማሪ እና የዋንጫ እንዲሁም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሆን አድርጎታል።
ተማሪ አላምረው በደብረ ታቦር ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በከፍተኛ ውጤት አጠናቋል።
ለስኬቱ መሠረት የሆነው ለጊዜ የሰጠው ልዩ ትኩረት፣ ትጋት እና ተከታታይ ጥረት መሆኑን የገለጸው አላምረው፣ ከልጅነቱ ጀምሮ በደረጃ ተሸላሚ እንደነበር እና በትጋት በመማሩ ለዚህ ውጤት መብቃቱን ተናግሯል።
“ከታላላቅ ወንድሞቼ የተማርኩት ፅናት፣ ከእናቴ እና ከመምህራኖቼ ያገኘሁት ድጋፍ ለውጤቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲልም ገልጿል።
ወደፊት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሀገሩ ጠቃሚና ችግር ፈቺ ባለሙያ ለመሆን እንደሚተጋ የገለጸው ወጣቱ፣ ትምህርቱንም በከፍተኛ ደረጃ ለመቀጠል እንደሚሰራ አስታውቋል።
የአላምረው ውጤት ለወጣቶች የትጋት፣ የቁርጠኝነት እና የዓላማ ጽናት ተምሳሌት መሆኑ ተጠቅሷል።



Source: GetuTemesgen








No comments yet.