#Ethioppia | የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አልፋ (Alpha TND & LTD ) እና ካፒታል( Capital electech ) ከተሰኙ ኢንጂነሪንግ እና ዕቃ አቅራቢ ተቋማት ጋር የ3 ቢሊየን ብር የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) እንዳሉት ፕሮጀክቱ በከተሞቹ ያለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝ በማድረግ ደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ ፕሮጀክት መሆኑን አመላክተው ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ መጠናቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአምቦ፣ ነቀምት እና አሶሳ ከተሞች የሚከናወን ሲሆን፣ በእነዚህ ከተሞች የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በማዘመንና በማጠናከር የአገልግሎቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ ያለመ ነው።
የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ፕሮጀክቱ 325 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ የኤሌክትሪክ መስመር የማሻሻያ ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ይህም የኔትወርኩን አቅም ከማሳደግ ባለፈ የኃይል መቆራረጥ እና የቴክኒክ ችግሮችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተጠቁሟል ።
በተጨማሪም 235 ትራንስፎርመሮች ላይ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራ የሚከናወን ሲሆን፣ ከእነዚህ 70 በአምቦ፣ 121 በነቀምት እና 44 በአሶሳ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
ዋና መቀመጫቸውን በጋና እና ሕንድ ያደረጉት የእነዚህ ተቋማት ተወካዮች በኤሌክትሪክ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ በዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ ግንባታና ማሻሻያ፣ እንዲሁም በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ዘርፍ ለተቋሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።
በቀጣይም በመሰል ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን በማዘመን፣ የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል እና የደንበኞችን ተጠቃሚነት በማሳደግ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ የጀመረውን ሥራ እንደሚያጠናክር ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ከወርልድ ባንክ በተገኘ 1.2 ቢሊዮን ብር እና 12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን፣ በአጠቃላይ በ3 ቢሊዮን ብር የሚከናወን ፕሮጀክት መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል፡፡



Source: GetuTemesgen









No comments yet.