#Ethiopia | የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ በወረዳ 11 ቡልጋሪያ በሚባለው አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት ከተሰበሰቡ ከ6 ሺህ በላይ የሺሻ ዕቃዎች እና 10 ኪሎ ግራም ካናቢስ አደንዛዥ ዕጽ በይፋ ማስወገዱን አስታወቀ።
በማስወገድ መርሃ ግብሩ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አመራሮች፣ የአስተዳደር ኃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የወንጀል መከላከልና የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎት መምሪያ አዛዥ ሺሻና አደንዛዥ ዕጽ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት እንደሚያስከትሉ እንዲሁም ለወንጀል መፈጸም መንስኤ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በመሆኑም ተመሳሳይ የማስወገድ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የክፍለ ከተማው የደንብ ማስከበርና የሰላም ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊዎች በበኩላቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ሕገ-ወጥ የሺሻና የአደንዛዥ ዕጽ ንግድን ለመከላከል የኦፕሬሽንና የቁጥጥር ሥራዎች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የወንጀል ምርመራ መምሪያ ተወካይ በበኩላቸው የተወገዱት የሺሻ ዕቃዎችና አደንዛዥ ዕጾች በልዩ የክትትልና የምርመራ ቡድን ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ ሥራ መሰብሰባቸውን ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይ የምርመራ መዝገብ መደራጀቱን አስታውቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም እርምጃውን በመደገፍ ወጣቶችን ከሱስ ለመታደግና የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ከፖሊስ ጋር ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።


Source: GetuTemesgen









No comments yet.