#Ethiopia | የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ቼን ሀይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በማሸነፉ ምክንያት ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የተላከውን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ተረክበዋል።
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በላከው በዚህ መልዕክት በፓርቲው ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነትና በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላም ብሔራዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና እንደሚረጋገጥ ሙሉ እምነት እንዳለው ገልጿል።
የምርጫው ውጤት የሕዝቡን ልባዊ ድጋፍ የሚያሳይ መሆኑን የጠቀሰው የቻይናው ገዥ ፓርቲ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግና መንግሥታዊ የልምድ ልውውጦችን በማስቀጠል በየትኛውም ሁኔታ የማይናወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የፓርቲ ለፓርቲ የመንግሥት ለመንግሥትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱም ፓርቲዎች ሀገር በቀል በሆኑ እሳቤዎችና መፍትሔዎች በመመራት ስኬት ማስመዝገብ መቻላቸውን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቻይና እያደረገች ላለው ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የቻይናው አምባሳደር ሚስተር ቼን ሀይ በበኩላቸው በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ያሉትን ድሎች በማድነቅ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ አዳዲስ የቻይና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በማዕድን በኢንዱስትሪ ፓርኮች በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰሳቸውንና ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል። ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በቀጣይም የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል በሁለቱ ገዥ ፓርቲዎች መካከል ያለው የላቀ ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen








No comments yet.