📌 በአመት እስከ 10 ሚሊዮን ብር ገቢ እያስገኘ ነው
#Ethiopia | የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና እና ሳይንስ ኮሌጅ የመማር ማስተማር እና የምርምር ስራዎችን ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት አርሶ አደሩንና የአካባቢውን ነዋሪ እያገዘ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አቸነፍ መላኩ ገለጹ።
ኮሌጁ በስድስት የትምህርት ክፍሎችና በተለያዩ የደረጃ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ከማስተማር ባለፈ፣ በስሩ በሚገኘው ክሊኒክ አማካኝነት ለአካባቢው አርቢዎች የእንስሳት ህክምና፣ የክትባትና የበሽታ መከላከል አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ በዘመናዊ መልክ በተደራጀው የወተት እርባታ ጣቢያው አማካኝነት በቀን ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ሊትር ወተት በማምረት ጥራቱን የጠበቀ ምርት በቅናሽ ዋጋ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ለአካባቢው ነዋሪዎች እያቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ በየቀኑ ወደ ስምንት መቶ የሚጠጉ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የእንስሳት እርባታ ጣቢያ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውና በሀኪም የታዘዘላቸው የሆስፒታል ታካሚዎችም በየቀኑ የወተት አቅርቦት እያቀረበ ይገኛል።
የጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ አያልሰው ተከስተ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በአካባቢው ገበያ የወተት ዋጋ እስከ ሰማንያ ብር በሚሸጥበት ወቅት ጣቢያው በሀምሳ ብር ዝቅተኛ ዋጋ ለነዋሪው ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ላይ ዋጋው ተሻሽሎ በ75 ብር እየቀረበ ይገኛል።
ጣቢያው ከዚህ የወተት ሽያጭ ብቻ በወር እስከ 450 ሺህ ብር ገቢ የሚያገኝ ሲሆን፣ በዚህ አመት ብቻ ከእንስሳት ሽያጭ ካገኘው ከ4.1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ጋር ተዳምሮ፣ በአጠቃላይ በአመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።
የተቋሙ የምርምር ስራዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመኑ መምጣታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አቸነፍ፣ በተለይም አርሶ አደሩን የወንድ ኮርማዎችን የመጠበቅ ወጪ የሚያድንና የሴት ጥጃዎችን ብቻ የመውለድ እድልን የሚያሰፋ የሰው ሰራሽ ማዳቀል ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ በማህበረሰቡ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው ፖሊሲና የምርምር ሰነድ ለዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት የቀረበ ሲሆን፣ ሂደቱን ጨርሶ ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚተላለፍ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ጣቢያው እስከ መቶ ሀያ የሚደርሱ ላሞችና ለምርምር ስራ የሚውሉ በጎችን የያዘ ሲሆን፣ በቀጣይም በደኑ ውስጥ ያለውን የንብ እርባታ ከማስፋፋት ባለፈ በአሳ እርባታ ዘርፍም ለመሰማራት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
በጌትነት ተመስገን
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ
#Ethiopia #GondarUniversity #GondarUniversity #CommunityService #AgriculturalResearch



Source: GetuTemesgen








No comments yet.