#Ethiopia | የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ እና የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የቱሪዝም ዘርፉን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሞተር ማድረግ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ ተገለጸ።
ይህንን ግብ ከዳር ለማድረስም መገናኛ ብዙኃን በየአካባቢው የሚገኙ ጸጋዎችን ፈጠራ በታከለበትና ማራኪ በሆነ አቀራረብ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት፣ አገሪቱ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በተሳለጠ መንገድ ለማስተዋወቅ የሚዲያው ሚና ወደር የለውም ብለዋል።
በቅርቡ የተመሰረተው የቱሪዝም ዘርፍ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ፎረም ዋነኛ ዓላማም ይኸው ገጽታን የመገንባት፣ የማስተዋወቅ እና የሽያጭ ሥራን በተናበበ መልኩ ለመምራት ነው። ሚዲያው የሰዎችን ቀልብ በሚስብ አግባብ መረጃዎችን ሲያቀርብ፣ ሰዎች እንዲጓጉ፣ እንዲመኙ እና የጉዞ ዕቅድ አውጥተው በጀት እንዲመድቡ ከፍተኛ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።
አቶ አለማየሁ እንደገለጹት፣ ማስተዋወቅ የቱሪዝም ስኬት ቁልፍ መሣሪያ ነው። ጎብኚዎች ወደ ስፍራዎቹ መጥተው ማኅበረሰቡ በጥሩ ሁኔታ ሲያስተናግዳቸውና የተደሰቱበትን የጉዞ ልምዳቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲያጋሩ የቱሪስቶች ፍሰት በሶስት እና አራት እጥፍ ይጨምራል ብለዋል።
በመላ አገሪቱ ከስምንት መቶ በላይ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ተለይተው እያንዳንዱ ወረዳ እና ዞን የየራሱን መዳረሻዎች እንዲያለማ አቅጣጫ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
መገናኛ ብዙኃን እነዚህን መረጃዎች ከሚኒስቴሩ “ላንድ ኦፍ ኦሪጂን” (Land of Origins)፣ ከ”ማይስ” (MICE)፣ እንዲሁም ከክልል የቱሪዝም ፕላትፎርሞች በተለያዩ ቋንቋዎች በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ይሁንና ጋዜጠኞች ጥሬ መረጃዎችን ከማሰራጨት ባለፈ መዳረሻዎቹን በአካል በመጎብኘትና በማጣጣም ስሜትን የሚስቡና ሕያው የሆኑ ዘገባዎችን ለተመልካች ማድረስ እንደሚገባቸው አቶ አለማየሁ በማሳሰብ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጌትነት ተመስገን
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen
#Ethiopia #EthiopianTourism #LandOfOrigins
#MICEEthiopia
Source: GetuTemesgen









No comments yet.