“ስለ እናት” የበጎ አድራጎት ድርጅት ለ1,500 ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ ጀመረ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja I የዘንድሮው የአለም የአፍሪካ ህጻናት ቀን “በአፍሪካ ለሚገኙ ደህንነቱና ንፅህናው የተጠበቀ አካባቢ ለሁሉም ህፃናት” በሚል አህጉራዊ መሪ ቃል በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

“ስለ እናት” የበጎ አድራጎት ድርጅት (SECO) በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አቅመ-ደካማ ወላጆችን ለመደገፍና ህጻናትን ከትምህርት ማቋረጥ ለመታደግ ያለመ የ1,500 ህጻናት የክረምት የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ ንቅናቄ በይፋ መጀመሩን አስታውቋል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ አብዱ እንደገለፁት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት፣ ጤናማና ንጹህ አካባቢ መፍጠር እንዲሁም መሰረታዊ የንጽህና ቁሳቁሶችን ማቅረብ ችሮታ ሳይሆን የማንኛውም ህጻን መሰረታዊ ሰብአዊ መብት መሆኑን አብራርተዋል።

አሁንም በአህጉሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት በውሃ ወለድ በሽታዎች እየተጠቁና ሴት ህጻናት ደግሞ በቂ የንፅህና መጠበቂያ ባለመኖሩ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እየቀሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ ማህበረሰቡ፣ መንግስታዊ አካላትና አለምአቀፍ አጋሮች ለWASH (የንጹህ ውሃ እና ንፅህና) ተደራሽነት መስፋፋት በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ድርጅቱ አሁን ላይ በአገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር በርካታ አቅመ-ደካማ ወላጆች ለልጆቻቸው መሰረታዊ የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላት ብርቱ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጿል።

ይህንን ክፍተት ለመሙላትም በመጪው አዲስ የትምህርት ዘመን የኢኮኖሚ አቅም ማነስ የትምህርት እክል ሊሆንባቸው የሚችሉ 1,500 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ህጻናትን በደብተር፣ በቦርሳና በሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶች ለመደገፍ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቆ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ በጎ አድራጊዎች በቁሳቁስም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

በሌላ በኩል ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን (25 ዓመታት) በህጻናት ጥበቃ፣ በቤተሰብ መልሶ ማቋቋም እንዲሁም በሴት የቤት መሪዎች ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበት ረገድ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጿል።

በመጪው ነሐሴ ወር የሚከበረውን የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ የድርጅቱን የህጻናት መቀበል አቅም በብዙ እጥፍ የሚያሳድግ የአዲስ ህንጻ ግንባታ የማስጀመሪያ መርሃ ግብርም አብሮ እንደሚከናወን ተገልጿል።

#ማህበራዊ






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2