ጎንደር – ብርሃኑ ነጋ እና ፍትፍቴ መሰንቆ

- Advertisement -
Sidebar AD

* ለባህል ጥበቃ የሚታትረው ቡቻች

#Ethiopia | ብርሃኑ ነጋ ይባላል። በጎንደር ግን ከስሙ ይልቅ “ቡቻች” በሚለው የልጅነት ስሙ ይታወቃል። ይህን ስም ያወጡለት እናቱ ናቸው።

የ31 ዓመቱ ቡቻች በአዘዞ ተወልዶ ያደገ ሲሆን፣ በፋሲለደስ ባህል ማዕከል ተወዛዋዥና ባህላዊ ከበሮ ተጫዋች ነው። በተጨማሪም የእስክስታዋ ንግሥት አርቲስት እንየ ታከለ የባህል ምግብ አዳራሽ የባንዱ ማናጀር ሆኖም ያገለግላል።

ዛሬ ግን በሌላ የፈጠራ ሥራው እየተደነቀ ነው። ከአባቱ ነጋ መኮንን የወረሰውን የባህል ፍቅር ወደ ተግባር በመቀየር፣ ፍትፍቴ መሰንቆ በእጁ እየሠራ ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል። ከዚህ በተጨማሪ ከበሮ፣ ዋሽንትና ክራር በመሥራት የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ለማስቀጠል እየተጋ ነው።

ወጣቶች ብዙዎች ሥራ ፍለጋ በሚባዝኑበት ዘመን፣ ቡቻች ግን የአባቶቹን ውርስ በእጁ እያኖረ ወደ ሥራና ፈጠራ መቀየሩ የሚያስደንቅ ነው። ይህ ጥረቱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን የጎንደርን እና የኢትዮጵያን የሙዚቃ ባህል ለትውልድ የሚያሸጋግር ውድ አስተዋፅኦ ነው።

በትጋት፣ በፅናትና በፈጠራ የተቀረጹት የቡቻች ነጋ እጅ ሥራዎች ከጎንደር ተነስተው ባህርዳርን አልፈው ዛሬ አዲስ አበባ ድረስ ደርሰዋል። በእጁ የሚሠሩ መሰንቆዎች፣ ዋሽንቶች፣ ክራሮችና ሌሎች ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በገበያ ተፈላጊ ሆነዋል።

በመጀመሪያ አንድ መሰንቆ በ2,500 ብር ይሸጥ ነበር። የሥራው ጥራት እየተሻሻለ፣ ፍላጎቱም እየጨመረ በመምጣቱ ዛሬ መደበኛው መሰንቆ እስከ 8,000 ብር ይሸጣል። በብረት መቃኛ (tuning pegs) እና በድምፅ ማጉያ ጃክ የተሟላ ዘመናዊ መሰንቆ ደግሞ 15,000 ብር ይደርሳል።

ይህ የዋጋ ለውጥ የሚያሳየው የእጅ ጥበቡ እውቅና እያገኘ መምጣቱን፣ የሥራው ጥራት ከፍ ማለቱን እና ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማዋሃድ ለተጫዋቾች የተሻለ አማራጭ ማቅረቡን ነው።

ቡቻች የሚሠራው መሣሪያ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ሙዚቃ ለቀጣይ ትውልድ የሚያሸጋግር ሕያው ቅርስ ነው። እንደዚህ ያሉ ወጣት የጥበብ ባለሙያዎች ሊበረታቱና ሊደገፉ ይገባል።

ትጋት፣ ጥረት፣ ፈጠራ እና ለባህል ያለው ፍቅር በእውነት የሚያስመሰግኑ ናቸው።

እንደ ቡቻች ያሉ ወጣቶች የባህላችን ሕያው አምባሳደሮች ናቸው።

ለቡቻች
ደውሉለት፤ እዘዙት

+251-918-138857
+251-904-365617

#ሼር # Share






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2