ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በገዳማትና በምእመናን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በማስመልከት ጥብቅ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ

- Advertisement -
Sidebar AD

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ በደቡብ ወሎ እና በሀድያና ስልጤ አህጉረ ስብከት በገዳማትና በምእመናን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በመኮነን አባታዊ መልእክት አስተላለፉ። ቅዱስነታቸው በደቡብ ወሎ ቦረና ወረዳ በግዮን አባይ ገዳመ አስቄጥስ በተፈጸመው ጥቃት የመነኮሳይያት ሕይወት ማለፉን፣ መቁሰልና የንዋያተ ቅድሳት ውድመት መድረሱን፤ እንዲሁም በሀድያና ስልጤ የአምልኮ ሥፍራ በኃይል መፍረሱን በከፍተኛ ሐዘን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በመግለጫቸውም ምንም ዓይነት ቁሳዊ ዝግጅት በሌላቸው መናንያን ላይ እጅ ማንሣት በታሪክና በእግዚአብሔር ፊት የሚያሳፍር ድርጊት መሆኑን ያሰመሩበት ቅዱስነታቸው፣ መንግሥትና የሕግ አስከባሪ አካላት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ለፍትሕ እንዲያቀርቡና የገዳማትን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ በጥብቅ ጠይቀዋል። በተጨማሪም መላው ሕዝበ ክርስቲያንና ኢትዮጵያውያን ለተጎዱት ወገኖች አስፈላጊውን ሰብአዊና መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ መልእክት ሙሉ ይዘት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!**

ገባሬ ሣህል እግዚአብሔር፥ ወይፈትህ ለኩሉ ግፉዓን፦ እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል።” (መዝሙር ፻፪፥፮)

ከሁሉ በማስቀደም በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም የምትኖሩ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችንን ሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ለሚከበረው፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ በእምነታቸው የጸኑትን ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን በመከራቸው መካከል እየተራዳ የእሳቱን ነበልባል እንደክረምት ውኃ ላቀዘቀዘበት፤ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የታመኑትንም እስከ ሰማዕትነት ፍጻሜ ድረስ የሚያጸና መሆኑን ለምንዘክርበት ታላቅ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የወንጌልን ብርሃን በማብራት፣ የሰላምን መንገድ በማስተማር፣ ፍትሕን በማጽናት፣ የተጨነቁትንም በማጽናናት፣ ሕዝብንና ሀገርን እየደገፈች የኖረች ናት።

በዚህ ቅዱስ ተልእኮ ውስጥም መናንያን መነኮሳት እና መነኮሳይያት ዓለምንና ከዓለም የሚገኘውን ጊዜያዊ ክብር፣ ጥቅም፣ ምቾትና የመሳሰሉትን በፈቃዳቸው ትተው፤ በየገዳማቱ በበአታቸው በጾም፣ በጸሎት ተወስነው፤ ሕይወታቸውን በትሕትና ለእግዚአብሔር በመስጠት፤ ስለ ራሳቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ሀገር፣ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ሰላምና ስለ ዓለም ደኅንነት በመዓልትና በሌሊት የሚጸልዩ የምድራችን በረከቶች ናቸው።

መስቀልን በተሸከሙ፣ ጸሎትን መከታ ባደረጉ፣ ለፍጥረት ሁሉ ምሕረትን በሚለምኑ፣ ራሳቸውን ለመከላከልም ምንም ዓይነት ቁሳዊ ዝግጅት በሌላቸው በእነዚህ መናንያን ላይ እጅን ማንሣት በእግዚአብሔር ዘንድ የተከለከለ፣ በታሪክ ፊትም የሚያሳፍር ድርጊት ነው።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በቦረና ወረዳ በግዮን አባይ ገዳመ አስቄጥስ ቅድስት አርሴማ፣ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ቂርቆስ የአባቶችና የእናቶች አንድነት ገዳም ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት በተፈጸመው ጥቃት የመናንያን መነኮሳይያት ሕይወት በግፍ መጥፋቱን፤ በርካቶች መቁሰላቸውን፤ በገዳሙና በንዋየ ቅድሳቱ ውድመት መድረሱን ከሀገረ ስብከቱ መግለጫ በከፍተኛ ሐዘን የሰማን ሲሆን፤ በተመሳሳይም በዚሁ ዕለት በሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት የአምልኮ ሥፍራ በኃይል መፍረሱና በምእመናን ላይ ጥቃት መድረሱ የሚያሳዝንና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው የተወገዘ ተግባር ነው።

በመሆኑም የጸሎት፣ የትምህርት፣ የሰላምና የመንፈሳዊ እሴት ማዕከል የሆኑትን ገዳማት መጠበቅ የአንድ ሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ክብርን፣ የሕግ የበላይነትንና የሀገር ሰላምን የማስጠበቅ ሓላፊነት ያላቸው በየደረጃው የሚገኙ ባለሥልጣናትና የሕግ አስከባሪ አካላት ጭምር እንደመሆኑ አሰቃቂ ጥቃት የፈጸሙት ተጠያቂዎች ለፍትሕ እንዲቀርቡ፤ ሌሎች ገዳማትና አድባራት ደኅንነታቸው እንዲጠበቅልን፤ ለተጎዱትም ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግልን ዛሬም አበክረን እንጠይቃለን።

በመጨረሻም ሕዝበ ክርስቲያንና መላው ኢትዮጵያውያን የጥቃት ሰለባ ከሆኑት ወገኖች ጋር በመንፈሳዊም ሆነ በሰብአዊ ድጋፍ አብራችሁ እንድትቆሙ ከአደራ ጭምር እያሳሰብን፤ በጽድቅ የሚፈርደው እግዚአብሔር አምላካችን ለተበደሉት ፍትሕን፣ ለቆሰሉት ፈውስን፣ በግፍ ሕይወታቸውን ለተነጠቁት ዕረፍተ ነፍስን፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ፍጹም ሰላምን ይስጥልን እያልን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ 18 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1