#Ethiopia | በጅማ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ከ5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ 1,876 የልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር ገልጸዋል።
አስተዳዳሪው ይህን ያስታወቁት በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ የተገነቡ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በይፋ በተመረቁበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
ለአገልግሎት ከተከፈቱት ፕሮጀክቶች መካከል መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የሁለተኛ ትውልድ ጤና ኬላ፣ የገበያ ማዕከል፣ የግብርና ግብዓት ማከማቻ መጋዘን፣ የወረዳ አስተዳደር ሕንፃ እና ሌሎች ማህበራዊ መሠረተ ልማቶች ይገኙበታል።
አቶ ቲጃኒ ናስር እንደገለጹት፣ የህብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲገነቡ ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል።
በመንግሥትና በህዝብ ትብብር የተገነቡት እነዚህ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል።
የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልከሪም አባራያ በበኩላቸው፣ በወረዳው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ግንባታቸው ከተጀመሩ 33 ፕሮጀክቶች ውስጥ 23ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መከፈታቸውን ገልጸው፣ ቀሪዎቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ ጥቅም እንደሚውሉ አስታውቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪ አቶ መሀመድ ዘይን ተማም በበኩላቸው፣ በወረዳው የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በመመለስ የኑሮ ሁኔታን እያሻሻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የዶዩ ቃጨማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱላሂ አባ ጀበል፣ በአካባቢው የተገነባው የግብርና ግብዓት ማከማቻ መጋዘን ከዚህ ቀደም ግብዓቶችን ለማግኘት ወደ አጎራባች ወረዳዎች በመጓዝ የሚባክነውን ጊዜና ወጪ እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።
የፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በዞኑ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የንግድና የግብርና አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማሳደግ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የበለጠ እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)



Source: GetuTemesgen









No comments yet.