#Ethiopia | የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከጤና ሚኒስቴር እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር «ጤናማ ምግብ ለአስተማማኝ ህይወት፣ አረንጓዴ ልማት ለነገ ትውልድ!» በሚል መሪ ቃል የክረምት በጎ አድራጎት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የባለሥልጣኑ ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን የኮፕ 32 (COP 32) አየር ንብረት ጉባኤን ከማገዝ ባሻገር አገር በቀል፣ ፍራፍሬ እና ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዕለቱም ከሰባት ነጥብ አንድ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ከምግብነት ባለፈ ለመድኃኒትነት ጭምር የሚጠቅሙ እንደ ማንጎ እና አቮካዶ ያሉ ከአምስት ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን አቅም ለማሳደግ እና የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን በራስ አቅም ለመሸፈን በምታደርገው ጥረት ውስጥ የመድኃኒትነት እጽዋትን መንከባከብ ትልቅ ድርሻ አለው።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለዕድገታቸው ተገቢውን ቋሚ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ይህንን አረንጓዴ ልማት ከምርምርና ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የሀገር ውስጥ መድኃኒት ማምረት አቅምን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፣ የጤና ሴክተሩ በበጎ ፈቃደኝነት መርሃ ግብሩ አጠቃላይ ከሁለት መቶ ኃምሳ ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን አንስተዋል።
ከአዲስ አበባ እስከ ቢሾፍቱ ባለው የፍጥነት መንገድ ዳርቻ የተጀመረው ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከአንድ ዓመት በኋላ ከፍተኛ የእጽዋት ሽፋን እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ የተተከሉትን ችግኞች በባለቤትነት ስሜት በመንከባከብ ለታለመለት ዓላማ ማብቃት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጌትነት ተመስገን
📷ከበደ መክብብ
#GreenLegacyEthiopia#Ethiopia
#Bishoftu #ClimateAction #HealthyLife
#COP32 #HealthSector #TreePlanting




Source: GetuTemesgen








No comments yet.