በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ የሚታዩ የክህሎትና የመዋቅር ችግሮችን ለመቅረፍ አዲስ የጋራ ስምምነት ተደረገ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja:-በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ የሚታዩ መዋቅራዊና የክህሎት ችግሮችን ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት እና የአባ ለታ አክቲንግ አካዳሚ በጋራ ለመስራት በዛሬዉ እለት ተፈራረሙ።

በአዲሱ አስተዳደራዊ መዋቅር ስር የሚገኙትን ብሔራዊ ቴአትር፣ ሀገርፍቅር ቴአትር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም (ባህል አዳራሽ)፣ ራስ ቴአትር እና የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትርን የሚያስተዳድረው ተቋሙ፤ ከግል ዘርፍ አጋሮች ጋር አብሮ ለመሥራት ባቀደው መሠረት ይፋዊ ስምምነቱን አድርጓል።

በስምምነቱ መሠረት የአስተዳደሩን የዘመናት የታሪክና የልምድ ክምችት ከአካዳሚው ዘመናዊና ፈጠራ የታከለበት የአሰልጠና ዘዴ ጋር በማዋሃድ በቴአትር፣ በሙዚቃ፣ በፊልምና ተዛማጅ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ሰፊ ስልጠናዎች በጋራ እንደሚሰጡ ተገልጿል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ወግ የሚያንፀባርቁ ጥበባዊ ሁነቶችንና ትላልቅ ፕሮዳክሽኖችን በጋራ በማዘጋጀት ለሕዝብ ለማቅረብ፣ እንዲሁም ከግጥም ምሽቶች እስከ ታላላቅ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሎች ድረስ ያሉ መድረኮችን ለማስፋፋት መታቀዱም ነዉ የተገለፀዉ።

የአባ ለታ አክቲንግ አካዳሚ ዋና መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሌንጮ ፍቅሩ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፤ አካዳሚው ከተመሠረተበት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በርካታ ወጣትና ህጻናት
ተማሪዎችን አብቅቶ ያስመረቀ ሲሆን፣ በተለይም በልጆች አክቲንግ ዘርፍ አበራች አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ሌንጮ አክለው እንደገለጹት፣ አካዳሚው እስካሁን በነበረው ጉዞ የቦታ፣ የሎኬሽን እና የትወና ቁሳቁሶች (Props) እጥረት ዋና ዋና ማነቆዎች እንደነበሩበት አስታውሰዋል።

ሆኖም ከአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ጋር የተደረገው ይህ ይፋዊ ስምምነት እነዚህን የሎጅስቲክስና የቦታ ችግሮች በዘላቂነት በመቅረፍ፣ የሰለጠኑ አዳዲስ ከዋክብትን ወደ ታሪካዊ የቴአትር መድረኮች ለማውጣት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: