#Ethiopia | የጎንደር ፋሲለደስ ባህል ኪነት የባህላዊ ሙዚቃ አልበም ትናንት በጎንደር ከተማ በተካሄደ ደማቅ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት በይፋ ተመረቀ።
በሙዚቃዊ፣ በሰላም ኢትዮጵያ እና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነጥበብ ቢሮ ትብብር የተዘጋጀው አልበም፣ የጎንደርን እና የአማራ ክልልን የባህል ሙዚቃ ለአለም አቀፍ አድማጮች ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመንግስት ተወካዮች፣ አርቲስቶች፣ የባህል ባለሙያዎች፣ አጋር ተቋማት፣ የሚዲያ ተወካዮችና በርካታ የጥበብ አፍቃሪዎች ተገኝተዋል። የጎንደር ፋሲለደስ ባህል ኪነትም የቀጥታ የሙዚቃና የውዝዋዜ ትርኢት በማቅረብ ታዳሚዎችን አስደስቷል።
በአልበሙ ውስጥ የቡድኑ ድምፃውያን ሕይወት እያሱ፣ እህተነሽ ፋንታ፣ ሰሎሞን ጥጋቤን ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ አባላት ተሳትፈዋል።
የሙዚቃ ዳይሬክተርነቱንም ሙዚቀኛ ምሳሌ ለገሰ መርተዋል። አልበሙ በባህላዊ የኢትዮጵያ መሳሪያዎች የተቀናበረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ተቀርጾ የድምፅ ማስተካከያውና ማስተሪንጉ በጣሊያን በሚገኘው ማክስሳውንድ ቫይብ ስቱዲዮ ተከናውኗል።
በዝግጅቱ ላይ የጎንደር ፋሲለደስ ባህል ኪነትን ከ50 ዓመታት በላይ የሚያስቆጥር ታሪክ የሚያሳይ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይም ለእንግዶች ቀርቧል። አውደ ርዕዩ የቡድኑን እድገት፣ ለኢትዮጵያ ሙዚቃና ትዕይንት ጥበባት ያበረከተውን አስተዋፅኦ እንዲሁም ያፈራቸውን ታዋቂ አርቲስቶች የሚያስታውሱ ታሪካዊ ፎቶግራፎችና ሰነዶችን አካቷል።
በዝግጅቱ ላይ የሙዚቃዊ ተወካይ ሲሳይ መንግስቴ፣ አልበሙ ከመደበኛ የሙዚቃ ስራ በላይ የኢትዮጵያን የባህል ሀብት ለማስጠበቅና ለአለም አቀፍ ተደራሽነት ለማብቃት የተደረገ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ስራ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ለአዲስ ትውልድ ለማስተላለፍ ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ#GondarFasilidesCulture #የጎንደርፋሲለደስባህልኪነት #EthiopianMusic #EthiopianCulture #Gondar #TraditionalMusic #Ethiopia



Source: GetuTemesgen









No comments yet.