ኢትዮጵያ እየተጠናቀቀ ባለው 2018 ዓ.ም ከ124 በላይ ዓለም አቀፍ ሜዳሊያዎች መገኘታቸውን ተገለጸ

- Advertisement -
Sidebar AD


‎#Ethiopia | ​በኢትዮጵያ የስፖርት ዘርፍ አዲስ እይታን በመፍጠር፣ ህጋዊና መዋቅራዊ ማዕቀፎችን በማጠናከር እንዲሁም በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማስተናገድ የ2018 በጀት ዓመት አመርቂና ስኬታማ ጊዜ የነበረ መሆኑ ተገለጸ።

‎​የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚያካሄደው የባህል፣ ጥበባትና ስፖርት ጥናትና ምርምር ጉባኤ እንዲሁም ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አቶ መክዩ መሀመድ እንደገለጹት፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ የታቀዱ ግቦችን በጋራ ለመገምገም እና ከክልል እስከ ፌደራል ያሉ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

‎አክለውም ዘንድሮ የስፖርት ልማት ስራዎች በተሻለ መንገድ የተፈጸሙበትና በአጠቃላይ የስፖርት ዘመን ተብሎ ሊወሰድ የሚችልበት የስኬት ዓመት እንደነበር ጠቁመዋል።

‎​የስፖርት ቤተሰቡ በተደጋጋሚ ያነሳቸው የነበሩ ህጋዊና አሰራር ነክ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ድኤታው፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትና ምሁራንን ያሳተፈ አዲስ የስፖርት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁንና አዋጁም ወደ ትግበራ መግባቱን አስረድተዋል።

‎ይህ አዲስ ፖሊሲ የመንግስትን አመራር ሰጪነት፣ ከ139 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህዝባዊ አደረጃጀቶችንና ማህበራትን አቅጣጫ፣ እንዲሁም የስፖርቱን እድገት የሚያፋጥነው የግል ባለሀብቶች ተሳትፎን በግልጽ የለየ አዲስ እይታ ይዞ መምጣቱንም አብራርተዋል።

‎​ስፖርት ከሜዳ ውድድር ባለፈ የህዝቦች ወንድማማችነትን የሚገነባ፣ ሰላምና አንድነትን የሚያጠናክር ትልቅ የሀገር ልማት መሳሪያ መሆኑን የገለጹት አቶ መክዩ መሀመድ፣ በዚህ ዓመት በተካሄዱ 420 የክልል አቀፍ እና 118 ሀገር አቀፍ ውድድሮች ከአስር ሺዎች በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል። እነዚህ መድረኮች የወጡ አትሌቶችን ከማፍራት ባሻገር ሰላምን በመገንባትና ህዝቦችን በማቀራረብ ረገድ የጎላ ሚና እንደነበራቸው አብራርተዋል።

‎​ህብረተሰቡን ንቁና ስፖርትን ባህል ያደረገ ለማድረግ በተሰራው ስራ የስፖርት አዘዋታሪው ህዝብ ቁጥር 24 በመቶ ወይም 32 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ሚኒስትር ድኤታው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ ከ45 ሺህ በላይ የስፖርት ፋሲሊቲዎች መገንባታቸውንና እነዚህንም በቴክኖሎጂ ዘመናዊ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‎​በአለም አቀፍና ቀጠናዊ ውድድሮች የሀገሪቱን ስም የሚያስጠሩ አሸናፊ ብሄራዊ ቡድኖችን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አትሌቶቻችን ከ124 በላይ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገባቸውን አቶ መክዩ መሀመድ አበክረው ገልጸዋል።

‎በተለይም በታዳጊዎች ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ45 ሺህ በላይ ታዳጊዎች በማሰልጠኛ ማዕከላት ውስጥ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

‎​በተጨማሪም የስፖርት ቱሪዝምን ለማበራታት በተደረገው ጥረት ከ29 በላይ ዓለም አቀፍ ውድድሮችና ኮንፈረንሶች በኢትዮጵያ መካሄዳቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታም ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

‎ስፖርት ለሀገር ጂዲፒ እና ለስራ እድል ፈጠራ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተጀመሩ ጥናቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።

‎​በመጨረሻም፣ በአዲሱ ፖሊሲ የባህል ስፖርት ልዩ ትኩረት ማግኘቱንና በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የባህል ስፖርት ፌስቲቫልን በበላይነት እንደምታዘጋጅ አቶ መክዩ መሀመድ ገልጸው፤ ላመጣው ስኬት ለስፖርት ቤተሰቡና ለመገናኛ ብዙሃን አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


‎ጌትነት ተመስገን
‎📷 ከበደ መክብብ

‎#EthiopianSports ​#EthiopiaSportPolicy ​#SportsDevelopment ​#Ethiopia​#YouthInSports ​#SportInspiration







Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1