የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ፍቃድ ባላቸው መገናኛ ብዙኃን፣ የንግድ መገናኛ ብዙኃን፣ የክልል እና የማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ሚዲያዎች እንዲሁም የበየነ-መረብ እና የውጭ ሚዲያዎች ላይ ከዚህ በኋላ የመጨረሻ አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወስድ የንግድ ፈቃዳቸው ወዲያውኑ የሚታገድበትና የሚዘጋበት አሰራር መዘርጋቱን ገለጸ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት ነሃሴ 7/2018 ዓ.ም ከ11 መንግስታዊ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት ነው።
ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ በዝርዝር ምን አሉ ?
” ከዚህ ቀደም እኛ የሰረዝናቸው ሚዲያዎች ሥራቸውን የሚቀጥሉበት ሁኔታ ነበር፤ ይህ የሆነው የንግድ ፈቃድ ቢሮ ፍቃዳቸውን ስለማይዘጋ ነበር። ከዚህ በኋላ እኛ ወዲያውኑ ፍቃዱን ስንሰርዝ የንግድ ፈቃድ ባስቸኳይ የሚታገድበት ወይም የሚዘጋበት ሁኔታ ይኖራል።
ይህ ብቻ አይደለም በአጠቃላይ የጸጥታ አካላት ይተባበራሉ፤ ምክንያቱም ሕገ-ወጥ ሚዲያ ኦፕሬት እንዲያደርግ አይፈቀድም።
ባለስልጣኑ ሕጋዊ አይደለም ብሎ፣ አሰራር ጥሷል ብሎ አስተዳደራዊ የመጨረሻ ውሳኔ ሲወስድ የተናበበ እርምጃ ነው ሁላችንም ተቋማት መውሰድ ያለብን። አንዱ በሰረዘበት ሁኔታ ሌላው ባለማወቁ ምክንያት እንዲቀጥል የሚፈቀድበት ሁኔታ ከዚህ በኃላ አይኖርም።
ከብሔራዊ ጥቅማችን ማረጋገጥ በተቃራኒ የቆሙ ሚዲያዎች ጥቂት የሚባሉ ቢሆኑም አሉ። እነሱን ስርዓት ማስያዝ፣ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ለባለስልጣኑ የተሰጠ ኃላፊነት ነው።
ያልተመዘገቡ በተለይ በበይነ-መረብ ሚዲያዎች ላይ በርካታ አሉ። ይህም የሆነው የአዋጅ ክፍተት ስላለ ነው። ይህ የሚስተካከል ይሆናል፣ በእኛ በኩል የአዋጅ ማሻሻያ ሰርተን አጠናቀናል፣ በቀጣይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያየዋል።
የህግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አንደኛው የአስተዳደራዊ እርምጃ ነው። ከአስተዳደራዊ እርምጃ ባለፈ ሕጋዊ ተጠያቂነትም አለ። በዚህ ጊዜ የጸጥታ ኃይሎች ያስፈልጋሉ።
ተቋማት ባልተገባ አስተያየት፣ ሚዛናዊ ባልሆነ መረጃ ላይ ተመስርቶ የስም ማጥፋት ይደርስባቸዋል። ከሀገር ሰላምና ደህንነት አንጻር የተለያዩ የስም ማጥፋት፣ ማጎደፍ ስራዎች ይሰራሉ።
በሃሰተኛ መረጃ ምክንያት የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍል ሰው አለ ፤ ተቋማት ሁሉ ባልተገባ መልኩ፣ ሙያው በሌለው፣ ስነ-ምግባሩ በሌለው፣ የሚዲያውን አዋጅ፣ የሀገሪቱን ሕግ በጣሰ መልኩ በሚፈጸሙ ንግግሮችና በሚሰሩ ፕሮግራሞች፣ በሚሰሩ ቃለ-መጠይቆች ስማቸው ይጠፋል ፤ እርምጃ የሚወስደው ባለስልጣኑ ብቻውን ሳይሆን ከፍትሕ አካላት ጋር እና ከተበደለው ወይም ደግሞ ስሙ ከጠፋበት ተቋም ወይም ደግሞ ባልተገባ እይታ እንዲታይ የተደረገው ተቋም ጋር አብሮ በመስራት ነው።
በተለይ በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚወጡ የተዛቡ፣ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች ሲኖሩ ብቻችንን አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ የምናቆመው ሳይሆን ከፍትሕ አካላትና የጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ይገባል ” ብለዋል።
@tikvahethiopia
Source: Yeneta Tube








No comments yet.