በቴዎድሮስ መኩሪያ
#Ethiopia | ከኢትዮጵያ ውጭ ይህ በዓል በእንግሊዝኛው “Feast of the Transfiguration” (የጌታችን የብርሃን መገለጥ በዓል) በመባል ይታወቃል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወጥቶ ፊቱ እንደ ፀሐይ ያበራበትንና ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ የሆነበትን (ማቴ 17፥1-8) ታሪክ መሠረት አድርጎ በመላው የክርስትና ዓለም ይከበራል።
በዓሉ መቼ መከበር ጀመረ? (ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ዳራ)
በምሥራቁ ዓለም (Early Eastern Church)፡ የደብረ ታቦር በዓልን ማክበር የተጀመረው በጣም ቀደም ብሎ ነው። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ326 ዓ.ም ገደማ) ንግሥት ዕሌኒ በእስራኤል በሚገኘው የደብረ ታቦር ተራራ ላይ ቤተ ክርስቲያን ካነጸች በኋላ፣ በዓሉን በተራራው ላይ ማክበር ተጀመረ። ከ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ደግሞ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በስፋት መከበር ጀመረ።
በምዕራቡ ዓለም (Western Church)፡ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች ይከበር የነበረ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፋዊ በዓል ሆኖ በይፋ እንዲከበር የታወጀው በ1456 ዓ.ም (15th Century) በሊቀ ጳጳሳት (Pope) ካሊክስተስ 3ኛ (Callixtus III) ነው። ይህም የክርስቲያን ሠራዊት በቤልግሬድ ጦርነት ኦቶማን ቱርኮችን ድል ያደረጉበትን መታሰቢያ ለማመስገን ነው።
አከባበሩ ምን ይመስላል?
ይህ በዓል በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ እና የአንግሊካን አብያተ ክርስቲያናት ይከበራል። አከባበሩም የየራሱ የሆነ የተለየ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታ አለው።
ሀ) በእስያ አህጉር (በተለይ በእስራኤል/ፍልስጤም)
በተራራው ላይ የካቶሊክ (Franciscan Church of the Transfiguration) እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ይገኛሉ። በበዓሉ ዋዜማ ከመላው ዓለም የመጡ ምዕመናን ድንኳን ተክለው፣ ሌሊቱን ሙሉ የጸሎት ትጋት (Night Vigil) በማድረግ ያሳልፋሉ። በዕለቱ ፀሐይ ስትወጣ ታላቅ ቅዳሴ ይቀደሳል። እንደኢትዮጵያውያን የችቦ መብራት ትውፊት ባይኖራቸውም፣ ሻማዎችን በማብራት የብርሃኑን መገለጥ ያስባሉ።
በአውሮፓ አህጉር (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ – ሩሲያ፣ ግሪክ፣ ሮማኒያ)
የበዓሉ ቀን፡ በነዚህ ሀገራት በዓሉ በግሪጎሪያን ካሌንደር ነሐሴ 6 (August 6) አሊያም እንደ ኢትዮጵያ ነሐሴ 13 (August 19) ይከበራል።
አከባበሩና የፍራፍሬ ቡራኬ ሥርዓት (Blessing of the First Fruits)፡ በግሪክ፣ ሩሲያ እና ሌሎች የባልካን ሀገራት በዓሉ እጅግ ደማቅ ነው። በኢትዮጵያ እናቶች “ሙልሙል ዳቦ” ጋግረው እንደሚያካፍሉት ሁሉ፣ በእነዚህ ሀገራት ደግሞ “የመጀመሪያ የፍራፍሬ ምርት” (በተለይም ወይን እና ፖም/Apple) ወደ ቤተ ክርስቲያን አምጥተው የማስባረክ ጥንታዊ ትውፊት አላቸው።
በዚህ ዕለት ካህናት ነጭ ወይም በወርቅ የተንቆጠቆጠ ልብሰ ተክህኖ ይለብሳሉ (የክርስቶስን የብርሃን ልብስ ለመወከል)። ምዕመናኑም ከተባረከው ፍራፍሬ እየተቋደሱ የክረምቱን ማለፍና የመከሩን መድረስ ያከብራሉ።
በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ (በካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት/አንግሊካን አብያተ ክርስቲያናት)
በእነዚህ አህጉራት በዓሉ በካቶሊክ፣ ኤፒስኮፓል፣ አንግሊካን እና ሉተራን አብያተ ክርስቲያናት ይከበራል።
ንደ አውሮፓ እና እስያ አደባባይ በሚወጣ ታላቅ ትዕይንት ባይሆንም፣ በዕለቱ ልዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት (Mass/Liturgy) ይካሄዳል። ስብከቱ የሚያተኩረው ክርስቶስ መለኮታዊ ክብሩን ስላሳየበት ሁኔታ እና ምዕመናን በሕይወታቸው መንፈሳዊ ለውጥ (Spiritual Transfiguration) ስለማምጣታቸው ነው።
የኢትዮጵያ የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል ከሌሎች በምን ይለያል?
ከላይ እንዳየነው ሃይማኖታዊ መሠረቱ (የክርስቶስ ብርሃን መሆን፣ የሙሴና የኤልያስ መገለጥ፣ የደመና መታየት) በመላው ዓለም አንድ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አከባበር ግን ሙሉ በሙሉ ልዩ እና እጅግ አስገራሚ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ማንነት አለው።
ጅራፍ ማጮህ፡ የክርስቶስን ድምፅ፣ ወይም በደብረ ታቦር የተሰማውን የአብን ድምፅ (“ይህ የምወደው ልጄ ነው…”) ለማሰብ። (ይህ በዓለም የትም የለም)
ሆያ ሆዬ / የልጆች ዝማሬ፡ ልጆች ሐዋርያትን ወክለው የምስራች ይዘው መንደር ለመንደር መዘመራቸውና መመረቃቸው።ሙልሙል ዳቦ፡ ምስጢሩን ለማየት ተራራ ላይ ለወጡት ሐዋርያት የተላከ ስንቅን ለማሰብ፣ እንዲሁም እንደ አውሮፓውያን የበኩር ፍሬ (ምስጋና) አቻ መሆኑ።
በደብረ ታቦር ከተማ (ፋርጣ)፣ ከአሸንድዬ (የልጃገረዶች ጨዋታ) እንዲሁም ከታላላቆቹ የሀገራችን መሪዎች የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ልደት ጋር ተቆራኝቶ መከበሩ በዓሉን የኢትዮጵያውያን የብሔራዊ ኩራት እና የኪነ-ጥበብ መገለጫ ያደርገዋል።
የደብረ ታቦር በዓል የሰው ልጅ ከተፈጥሮ (ክረምት ወጥቶ ብርሃን ሲፈነጥቅ) እና ከፈጣሪው ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት የሚያሳይ ዓለም አቀፋዊ የክርስትና በዓል ነው።
ይሁን እንጂ ወደ ደብረ ታቦር ከተማ ተጉዞ፣ አሸንድዬን እያዩ፣ የጅራፉን ጩኸት እየሰሙ፣ ሙልሙል እየቀመሱ እና በታላቋ ርዕሰ አድባራት ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ማክበር የሚሰጠው ስሜት፣ ከማንኛውም የዓለም ክፍል የላቀና ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለው
ውብ ሥርዓት ነው!
ያመት ሰው ይበለን!!
Source: GetuTemesgen









No comments yet.