የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል የቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት እየተስተዋለ ያለውን ያልተገባ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪና የመስመር ማሳጠር ችግሮችን ለመቅረፍ የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።
ቢሮው የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍን በማጥናትና በማስወሰን ረገድ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት የገለጹት የቢሮው የስራ ሃላፊ፣ የታሪፍ ተግባራዊነቱንም በቅርበት እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በከተማዋ ከሚንቀሳቀሱ ከ15 ሺህ በላይ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪዎች መካከል አብዛኞቹ በህጋዊ መንገድ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም፣ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ግን ህዝቡን ሲያማርሩ እንደሚስተዋል ተመልክቷል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ባለፈው አመት ብቻ ከ120 ሺህ በላይ በሚሆኑ አሽከርካሪዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል ።
ከእነዚህ አሽከርካሪዎች መካከል 25 በመቶ ያህሉ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ የተገኙ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ መስመር በማሳጠርና መሰል ጥፋቶች የተመዘገቡባቸው ናቸው ብለዋል።
እርምጃው በገንዘብ ቅጣት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ጥፋቱ ተደጋጋሚ ሆኖ ሲገኝ እስከ ስራ ማገድ የሚደርስ ጥብቅ ውሳኔዎች እየተወሰዱ መሆኑም ተገልጿል።
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ቢሮው በ9417 ነጻ የጥቆማ መስመር አማካኝነት ከህዝቡ መረጃዎችን እየተቀበለ ይገኛል።
ህብረተሰቡ የታሪፍ ጭማሪ ሲያጋጥመው የአሽከርካሪውን ታርጋ ቁጥርና በመያዝ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።
Via Ethio fm
Source: Yeneta Tube








No comments yet.