የጉዞ ማስታወሻ
ተስፋዬ እሸቱ (ረዳት ፕሮፌሰር)
#Ethiopia | ከሰሞኑ ጣሊያን በነበረን የትያትር ሥልጠና “I am from a place where…” የሚል የጌም መልክ ያለውና ወደዋነው ጉዳይ የሚያንደረድር አንድ ጨዋታ እንጫወት ነበር።
አጨዋወቱ ቀላል ነው። በክብ ተቀምጠን አንድ ሰው መሀል ይቆማል። “I am from a place where…” ብሎ ከመጣበት ማኅበረሰብ፣ ባህል ወይም የኑሮ ልምድ ጋር የሚያያዝ አንድ ነገር ይናገራል።
የተናገረውን ሐሳብ የሚጋሩ ሰዎች ከወንበራቸው ተነስተው ቦታ ይቀያየራሉ። ቦታ ያጣው ደግሞ መሀል ቆሞ የራሱን “I am from a place where…” ይናገራል፤ ጨዋታውም በዚሁ መልኩ ይቀጥላል።
አብዛኛውን ጊዜ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ከእኔ ልምድ ጋር የማይገጥሙ፣ እኔም የማልጋራቸው ስለነበሩ ከመቀመጫዬ አልተነሳሁም። ዝም ብዬ የሚሉትን እከታተል ነበር። ድንገት አንዷ አሜሪካዊት፣ “የመጣሁት በነጭና በጥቁር መካከል ኢፍትሐዊነት ካለበት ቦታ ነው” አለች። ብዙዎቹ ተነሱ።
እኔም አሰብኩ። በአገሬ የነጭና የጥቁር መከፋፈል በዚያው መልክ ባይኖርም፣ እኔ ጥቁር ነኝ። ስለጥቁር ማንነትና መብት የተነሳ ጉዳይ ነውና “እኔ ታዲያ እዚህ ተቀምጬ ምን እሠራለሁ?” ብዬ ከመቀመጫዬ ተነሳሁ።
ስለጉዳዩ እያሰብኩ ስለነበር ዘወር ስል ቦታዬ ተይዟል! መሀል ቆሜ “ምን ልበላቸው?” እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። ሁሉም ዓይን ዓይኔን ሲመለከተኝ፦
“I am from a place where our airline is part of our identity.”
“የመጣሁት እንደ ዓይናችን ብሌን የምናየው አየር መንገዳችን የማንነታችን አካል ከሆነበት አገር ነው።” እንደማለት ነው።
ዙሪያዬን አየሁ።
የሚነሳ አጣሁ!
አንድም የጨዋታው ተሳታፊ ከመቀመጫው አልተነሳም። ግራ ገባኝ። እኔም እዚያው መሀል ቆሜ ቀረሁ። ምንም እንኳ የጨዋታው ሕግ መጠየቅን ባይፈቅድም፣ አለመነሳታቸው ቆረቆረኝ። የመጣው ይምጣ ብዬ፦
“ለምን አልተነሳችሁም?” አልኳቸው።
መልሳቸው የተለያየ ነበር። ለአንዳንዶቹ አየር መንገድ በዋናነት የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው። አንዳንዶቹማ “የእኛ” የሚሉት ተወዳዳሪ ብሔራዊ አየር መንገድ እንኳ የላቸውም። ለሌሎቹ ደግሞ የሀገራቸው መለያ ቢሆንም፣ እስከ “የማንነቴ አካል ነው” የሚያስብል ግንኙነት ከአየር መንገዳቸው ጋር አልነበራቸውም።
ምናልባት “የመጣሁት ሽማግሌዎች ከሚከበሩበት ቦታ ነው” ብዬ ቢሆን ኖሮ ከወንበራቸው የሚነሱ ይኖሩ ነበር። “የመጣሁት ቤተሰብ ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው ማኅበረሰብ ነው” ብል፣ ወይም “የመጣሁት እንግዳ በክብር ከሚቀበልበት ቦታ ነው” ብል፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሰዎች ሐሳቡን ሊጋሩኝ ይችሉ ነበር። እነዚህ በብዙ ማኅበረሰቦች የሚጋሩ እሴቶች ናቸውና።
አየር መንገድን ከማንነት ጋር ሳገናኝ ግን ሐሳቡን የሚጋራኝ አጣሁ።
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ውስጤ ቀረ።
እንዴት ነው አንድ የንግድና የመጓጓዣ ተቋም ከተራ ተቋምነት አልፎ የሕዝብ የጋራ ማንነትና ኩራት አካል የሚሆነው?….መልሱ “የሀገራችንን ባንዲራ ይዞ ስለሚበር” ብቻ አይደለም። እንዲያውም ይህ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ የተሰጠ ልዩ ነገር አይደለም። በዓለም ላይ ብዙ flag carriers የሀገራቸውን ባንዲራ፣ ብሔራዊ ቀለማት ወይም ሌሎች የሀገር ምልክቶች በአውሮፕላኖቻቸው ላይ ይዘው ይበራሉ።
ታዲያ የእኛን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?….
ለእኔ ልዩነቱ ባንዲራውን መሸከሙብቻ አይደለም። ያንን ባንዲራና “Ethiopian” የሚለውን ስም ከተቋማዊ ቀጣይነት፣ ከውድድርና ከስኬት ጋር ማያያዝ መቻሉ ነው። የኢትዮጵያን ስም ይዞ ለዓመታት ተወዳድሯል።
በውድድሩ ውስጥ ብቻ አልቆየም፤ አድጓል፣ መዳረሻዎቹን አስፍቷል፣ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ገበያ ውስጥም ተወዳዳሪ ተቋም ሆኗል። በሀገራችን የተለያዩ ዘመናት፣ መንግሥታትና ፈተናዎች ሲፈራረቁ፣ እሱ ግን ትውልድ ተሻግሮ “Ethiopian” የሚለውን ስም ይዞ ቀጥሏል። ምናልባት የማንነት ጉዳዩ የሚጀምረውም እዚህ ላይ ነው። ማንነት በስም፣ በባንዲራና በቀለም ብቻ አይገነባም፤ በታሪክ፣ በቀጣይነት፣ በስኬትና በጋራ ትውስታም ይገነባል።
ስለዚህ በሌላ ሀገር አየር ማረፊያ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩን ጭራ ከሩቅ ስናይ፣ የምናየው ቀለም ብቻ አይደለም። ከዚያ ቀለም ጀርባ ያለውን ስም፣ ታሪክ፣ ቀጣይነትና ስኬትም ነው። በዚህም አየር መንገዳችን ከተራ የመጓጓዣ ተቋምነት አልፎ የጋራ ትውስታችንና ኩራታችን አካል ሆኗል። በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያገኘው ቦታም ከዚህ የመጣ ነው።
ከጨዋታው በኋላም ለሥልጠናው ከተለያዩ ሀገራት ለመጡት የትያትር ባለሙያዎች ደረቴን ነፍቼ ነገርኳቸው፤ አየር መንገዳችን ከA ወደ B የሚያደርሰን የመጓጓዣ ተቋም ብቻ አይደለም።
“Ethiopian” የሚለውን የሀገሬን ስም ይዞ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መልክ በሰማይ ላይ የሚዞር፣ ታሪካችንን ሰማይ ላይ ያተመ ስማችን ነው፡፡ መቸስ ከዚህ በኋላ የኢትዮዽያን አየር መንገድ ሲያዩ እንደ ቀላላ አየር መንገድ እንደማይወስዱት ተስፋ አለኝ፡፡
አዎ፣ እኔ ሁሌም እንዲህ እላለሁ፦
“I am from a place where our airline is part of our identity.”
የመጣሁት አየር መንገዳችን የማንነታችን አካል ከሆነበት አገር ነው።
ደህና አምሹ!



Source: GetuTemesgen







No comments yet.