ብሔራዊ ባንክ ሕገወጥ ያላቸውን 17 ድርጅቶች ይፋ አደረገ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኅብረተሰቡ፣ የዳያስፖራ አባላትና ደንበኞች ፈቃድ የሌላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎችና ሕገወጥ የሐዋላ መረቦችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥብቅ ማሰሰቢያና ማስጠንቀቂያ አስተላለፈ።

ባንኩ ባወጣው መግለጫ እነዚህ ሕገወጥ ተግባራት በኢትዮጵያ ሕግ በጥብቅ የተከለከሉ መሆናቸውን ጠቁሞ በእነዚህ መንገዶች ገንዘብ መላክም ሆነ መቀበል ደንበኞችን ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ፣ ለክፍያ መዘግየት፣ ለባንክ ሒሳብ ዕገዳና ለሕግ ተጠያቂነት እንደሚያጋልጥ አስገንዝቧል።

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የገንዘብ ዝውውር እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሕገወጥ መንገዶችን መጠቀም ላኪዎችንም ሆነ ተቀባይ ቤተሰቦችን ለአስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች ሊዳርግ ስለሚችል ዜጎች ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውን አማራጮች ብቻ እንዲጠቀሙ መክሯል።

​በተጨማሪም ብሔራዊ ባንኩ ወደ ኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ያልተሰጣቸውንና ሕገወጥ ያላቸውን 17 ድርጅቶች ስም ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሠረት አዱሊስ መኒ ትራንስፈር (Adulis Money Transfer)፣ አማል ኤክስፕረስ (Amal Express)፣ አማል ዩኤስኤ (Amal USA)፣ አማና ኤክስፕረስ (Amana Express)፣ አቫንቲ (Avanti)፣ አዋሽ ዳይሬክት (Awash Direct)፣ ባካል መኒ ትራንስፈር (Bakaal Money Transfer)፣ ጁባ ኤክስፕረስ (Jubba Express)፣ ራስሚ ፔይ (Rasmy Pay)፣ ረማድ ፔይ ወይም ረማዳ ፔይ ካህ (Ramad Pay / Ramada Pay (Kaah))፣ ሽጌይ መኒ ትራንስፈር (Shgey Money Transfer)፣ ታጅ ፋይናንሻል ሰርቪስ (Taaj Financial Service)፣ ታሳ ፔይ (Tasa Pay)፣ ተወከል መኒ ሰርቪሰስ (Tawakal Money Services)፣ ዩኤስዋየር (USwyre)፣ ወርልድ ዳይሬክት ሊንክ (World Direct Link) እና ዞላ (Zola) የተባሉት ድርጅቶች ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ደንበኞች የገንዘባቸውን ደኅንነት ለመጠበቅና በአስተማማኝ ሁኔታ መድረሱን ለማረጋገጥ ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸውን ወኪሎች ብቻ እንዲጠቀሙ ያበረታታው ባንኩ፣ ማናቸውንም ዝውውር ከመፈጸማቸው በፊት የተመረጠው ድርጅት ሕጋዊነት በባንኩ ይፋዊ ድረ-ገጽ (https://nbe.gov.et/mta/) ገብተው ማረጋገጥ እንደሚችሉ አሳውቋል።

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: