ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ደህንነትን ለማስከበር በናይሮቢ በተካሄደ ውይይት ተሳተፈች

- Advertisement -
Sidebar AD

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ እየጨመረ የመጣውን የባህር ላይ ደህንነት ስጋት ለመከላከል በናይሮቢ በተካሄደ ቀጠናዊ ውይይት ላይ መሳተፏን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

የሁለት ቀን ስብሰባው በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር እና የመረጃ ልውውጥ ለማጠናከር ያለመ ነው። በውይይቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የየመን፣ የጅቡቲ እና የሶማሊያ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ውይይቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ቢሮ ያመቻቸው ሲሆን፣ ለአሰራር ትብብር እና ለባህር ላይ ውንብድና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ላይ አተኩሯል።

የአውሮፓ ሕብረት፣ ኢንተርፖል፣ የዓለም አቀፍ የባህር ኃይል ድርጅት እና ኢጋድ ለውይይቱ ድጋፍ አድርገዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ባለሥልጣን ካፒቴን ክብሩ መስፍን፣ የባህር ደህንነት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። የአገሪቱ አብዛኛው ንግድ በጅቡቲ በኩል የሚያልፍ በመሆኑ በባህር መስመሮች ላይ የሚፈጠሩ መስተጓጎሎች የመርከብ እና ኢንሹራንስ ወጪን እንደሚጨምሩ አብራርተዋል።

ካፒቴን ክብሩ አክለውም፤ በባህር ባለሥልጣናት እና ሕግ አስከባሪዎች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህር ኃይል መረጃ ማዕከል ለማቋቋም ጥረት እያደረገች እንደሆነም ገልጸዋል።

የጂቡቲ የባህር ኃይል ባለስልጣን አብዱራሂም መሐመድ አሊ በበኩላቸው፣ የቀጠናው ደህንነት የጋራ ስጋት በመሆኑ ሀገራት የቅርብ የመረጃ ልውውጥ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው ውይይቱ በመካከለኛው ምስራቅ ክፍሎች ያለውን የባህር ላይ ውጥረት እና የመርከብ ደህንነት ስጋት ለመከላከል ትልቅ እድል ይፈጥራል።

#አሐዱ_ሬዲዮ


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: