የህዝብ ክብረ በዓላት ባህላዊ እሴቶችንና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበሩ ተገለጸ

- Advertisement -
Sidebar AD


‎#Ethiopia | ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔና የብዙሃ ባህል ባለቤት እንደመሆኗ መጠን ለዘመናት ያዳበረችውን አብሮ የመኖር እሴት አጠናክራ እንደምትቀጥል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ነፊሳ አልማሃዲ ገለጹ።

‎ክብርት ሚኒስትሯ የህዝብ ክብረ በዓላትን አስመልከተው በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፣ የሀገራችን የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ስብጥር የጥንካሬያችን ምስጢር በመሆኑ ይህንን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

‎ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የባህል ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ምቹ የህግ ማዕቀፎችንና መመሪያዎችን ዘርግቶ እየሰራ ይገኛል።

‎​እንደ ክብርት ሚኒስትሯ ማብራሪያ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን የአዋጅ ቁጥር 1334/2016 እና የህዝብ ክብረ በዓላት ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 1116/2018 መሠረት በማድረግ ዘርፉን በታቀደ መንገድ የመምራት ስራ ተከናውኗል።

‎በዚሁ መሠረት በ2018 በጀት ዓመት ለሶስት ወራት በዘለቀው የባህል ንቅናቄ ከ46 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ማሳተፍ የተቻለ ሲሆን፣ ሂደቱም በውጤቱ የላቀ ስኬት ያስመዘገበ ነበር። ይህ አፈፃፀም አገር በቀል እውቀቶችን በማጉላት፣ የማህበረሰቡን ሚና በማሳደግና ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

‎​ይህ የጀመረው ጥረት በ2019 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ክብርት ነፊሳ አልማሃዲ፣ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ የሚከበሩ በዓላት በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበሩ ተናግረዋል።

‎በተለይም ለመጪው የጳጉሜ 4 «የህብር ቀን» እና በየክልሎቹ ለሚካሄዱ በዓላት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም፣ እነዚህ በዓላት የሰዎችን ልዩነት እንደ ፀጋ በመቀበል፣ መቻቻልንና አካታችነትን በማስፈን፣ እንዲሁም አንድ የጋራ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

‎​በመጨረሻም የህዝብ ክብረ በዓላት ማህበራዊ ትስስርን ከመፍጠር ባሻገር የቱሪዝም ፍሰትን በመጨመር፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና የአካባቢውን ንግድ በማንቀሳቀስ ረገድ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች እንዳሏቸው ክብርት ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። በመሆኑም ህብረተሰቡ እነዚህን በዓላት ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ የአብሮነትና የሰላም መገለጫ አድርጎ እንዲያከብራቸው ጥሪ አቅርበዋል።

‎በጌትነት ተመስገን

‎Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ ​#MoCS #CultureAndSportMinistry ​#Ethiopia ​#EthiopianCulture ​#UnityInDiversity ​#Pagume





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2