#FastMereja I ኢትዮ ቴሌኮም “ቀጣዩ አድማስ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028” የተሰኘውን የሶስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታውን ሁለተኛ ዓመት የ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ የቢዝነስ እቅድ ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የ36.7 በመቶ ወይም የ79.2 ቢሊዮን ብር እድገት በማስመዝገብ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢውን 295 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን ገልጻል። በተጨማሪም 253.7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
በአዲሱ የበጀት ዓመት እቅድ መሰረት የኩባንያው አጠቃላይ የቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር በ6.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ ተጠቃሚዎችን 96.2 ሚሊዮን ያደርሰዋል። የሞባይል ዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ16.5 በመቶ በማሳደግ 60.01 ሚሊዮን የማድረስ ግብ ተይዟል።
በሌላ በኩል የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን 67.69 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ በቴሌብር የሚከናወኑ ንቁ ግብይቶች መጠን 7.4 ትሪሊዮን ብር እንዲሁም የግብይት ብዛት 4.99 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። በቴሌብር በኩል የሚሰጠው የዲጂታል አነስተኛ ብድር አቅርቦትም ከ19.51 ቢሊዮን ብር ወደ 35.04 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ይደረጋል።
መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ በበጀት ዓመቱ 5,417 አዳዲስ የ4ጂ ጣቢያዎችን በመገንባት የ4ጂ ኔትወርክን ሽፋን ከ82.23 በመቶ ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። የ5ጂ አገልግሎትንም ተደራሽ የሚደረግባቸውን ከተሞች ቁጥር ከ33 ወደ 73 በማሳደግ የጣቢያዎቹን ቁጥር 648 ለማድረስ ዝግጅት ተጠናቋል።
ኩባንያው ዲጂታል አካታችነትን ለማረጋገጥ 1 ሚሊዮን ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የ”ዘኔክሰስ” ስማርት ስልኮች ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ለአገራዊ ልማትም 43.1 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል እና 83.8 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የግብር ክፍያ ለመንግስት ገቢ ለማድረግ አቅዷል።
Source: FastMereja









No comments yet.