♦️
♦️”የሶስት አስርት ዓመታት ልፋቴንና ድካሜን ቆጥሮ ይገባሃል ብሎ በክብር ኒሻን በጡረታ ሲያሠናበተኝ ማየት ለእኔ ትልቅ ደስታ ብቻ ሳይሆን ታሪክም፣ዕድልም ነው”
ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ
የመጀመሪያ አፍሪካዊ በመሆን የወርቅ ሜዳልያን ያፈራችውን ጀግናዋን አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን፣በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈችውን ጀግናዋን ፋጡማ ሮባን፣የሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ አሸናፊዋን ጀግናዋን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን፣በኦሎምፒክና በአለም ሻምፒዮና ሀገሩን ያኮራው ጀግናው አትሌት ስለሺ ስህንና በኢትዮጵያ አቴሌቲክስ ታሪክ በአሠልጣኝነት በወርቅ ያሸበረቀ ውጤት ኤንዲመዘገብ ለሀገሩ ታሪክ የሠራውን ከበርካታ ታላላቅና ውጤታማ አትሌትች ጀርባ የሚገኘው ረዳት ኮሚሽነር አሠልጣኝ ሁሴን ሸቦን ለሀገራችንና ለዓለም ያበረከተው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የጀግና የክብር ኒሻንና የማዕረግ ዕድገት ለባለውለታዎቹ በመስጠት አክብሯል።
በዚህም መሠረት ውጤታማው አሰልጣኝ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አቴሌት ስለሺ ስህን፣አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የክብር ኒሻንና የማዕረግ ዕድገት ተበርክቶላቸዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ለረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ የጀግና የክብር ኒሻን አበርክቶለታል፤ ኮሚሽኑ የክብር ኒሻን ሲያበረክት ይሄ የመጀመሪያ አይደለም፤ከዚህ በፊትም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቁ ሽልማት የሆነውን የክብር ኒሻን ለአራት ሠው ማለትም ለረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ለአትሌት ስለሺ ስህንና አሁን በመጨረሻ ለረዳት ኮሚሽነር አሠልጣኝ ሁሴን ሼቦ አበርክቷል።
ከአንድ ዓመት ከጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ጋር የረዳት ኮሚሽነርነት የማዕረግ ዕድገት ያገኘው አሠልጣኝ ሁሴን ከሶስት አስርት ዓመታት ለዘለቀውና በውጤት ላሸበረቀው ስኬቱ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የአሠልጣኞች ታሪክ ትልቁ ሽልማት የሆነውን የክብር ኒሻን ተበርክቶለታል።
በርካታ የክብር ሽልማቶችና ማዕረጎች የጎረፉለት፣በ7 ኦሎምፒክና በ12 የአለም ሻምፒዮና በመሳተፍ ታሪክ የሠራው ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦን በክብር ኒሻኑ ዙሪያ የተሠማውን ስሜት እንዲያጋራን ወደ እጅ ስልኩ ደውዬ ከዚህ በታች ያለውን ቆይታ አድርገናል።
♦️የጀግና የክብር ኒሻን መሸለሙ ስለፈጠረበት ስሜት…
“እንዳንዴ ቃላት ስሜትህን መግለፅ ያቅታቸው የለ?በተደረገልኝ ነገር እጅግ በጣም በመደሠቴ በቃ እኔም እንደዛ ነው የሆንኩት፤የልቤን መግለፅም፣በቃላት መናገርም ከብዶኛል፤በቃ ከዚህ በፊት ብዙ ሽልማቶችን፣ክብሮችን አይቻለሁ በዛም በጣም ተደስቻለሁ፤የአሁኑን ስሜቴን ግን መቆጣጠርም መግለፅም እጅግ በጣም ከብዶኛል፤ለሶስት አስርት ዓመታት ለእናት ክለቤም፣ለሀገሬም ብሎም ለዓለም ያበረከትኩትን ቆጥረው ለዚህ ታላቅ ከብር ስላበቁኝ በጣም ደስ ብሎኛል፤በጣምም ነው የማመሠግነው።”
♦️ላለፉት 30 ዓመታት ፊሽካ ከእጄ፣ እግሬም ከልምምድና ከውድድር ቦታ አንደም ቀን ርቆ አያውቅም
“በጣም የሚገርምህ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ፊሽካ ከእጄ እግሬም ከልምምድና ከውድድር ቦታ ርቆ አያውቅም፤በፍፁም ዲሲፒሊንና ሀገራዊ ፍቅር አንድም ቀን ከአትሌቶችና ከልምምድ ሜዳ ጠዋትም ማታም ሳልርቅ ሙሉ ህይወቴን ለአትሌቲክስ በመገበር ነው ያሳለፍኩት፤የስኬታማነቴ ምስጢርም ይሄው ነው፤ሌላው በፍፁም ዲሲፕሊን መስራቴ ጎልቶ ይጠቀሳል፤ከምስጋና በስተቀር አንድም ቀን የክስ ቻርጅ፣ማስጠንቀቂያ ወይም የቅጣትና የዕግድ ደብዳቤ ፋይሌ ውስጥ ገብቶ አያውቅም፤ኮሚሽኑ ዝም ብሎ አይደለም ይሄንን ክብር የሠጠኝ፤ ይሄንን ሁሉ አገናዝቦና ፈትሾ ነው፤ይበልጥ ደስተኛ ያደረገኝም ይሄው ነው፤ሌሎችም እንደ እኔ ከሠሩና ውጤታማ ከሆኑ ከፈጣሪ በታች ሠውም፣ተቋምህም ውለታህን ቆጥሮ ይከፍልሀል”
♦️በመጨረሻ…
“እናት ክለቤ በመጨረሻ የሠጠኝ ክብርና ኒሻን የእኔ ብቻ አይደለም፤ለሀገራቸው የለፉ፣የደከሙ አሠልጣኞችም ነው፤እናት ክለቤ የሶስት አስርት ዓመታት ልፋቴንና ድካሜን ቆጥሮ ይገባሃል ብሎ በክብር ኒሻን በጡረታ ሲያሠናበተኝ ማየት ለእኔ ትልቅ ደስታ ብቻ ሳይሆን ታሪካም፣ዕድልም ነው፤ይሄ እንዲሆን አብረውኝ የደከሙትን፣ይገባዋል ብለው ለዚህ ክብር ያጩኝን በሙሉ አመሠግናለሁ።
✍️ በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ
(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከከናዳ ቶሮንቶ

Source: GetuTemesgen




![ለካ ከፈጣሪ በታች ሠውም[ድርጅትም]ልፋትህንና ውለታህን ቆጥሮ እንደሚከፍል እናት ክለቤ በተግባር አሳይቶኛል](https://new.yenevibe.com/storage/2026/06/725634172_1473466081492055_8206775495693374881_n-750x1125.jpg)




No comments yet.