#Ethiopia | በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ውስጥ ለሳምንታት ሰፍረው የነበሩ ከ1,000 በላይ የማላዊ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያስችል የሰነድ ማጣራት ሂደት መጠናቀቁ ተገለጠ።
የማላዊ ኤምባሲ ዜጎቹን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለማጓጓዝ የሚያስችሉ አውቶቡሶችን ያዘጋጀ ሲሆን፣ እስካሁንም በደርባን ሸርዉድ አካባቢ የትራንስፖርት እገዛ ሲጠባበቁ ከነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ማላውያን መካከል የ1,140 ሰዎችን ማንነት ማረጋገጥ ተችሏል። በጥቅሉ ለጉዞው ቅድሚያ የተሰጣቸው ለሕፃናትና ለሴቶች መሆኑ ታውቋል።
የኳዙሉ-ናታል ግዛት ሃላፊ ታሚ ንቱሊ እንደገለጹት፣ የመመለስ ሂደቱ ሰብአዊ መብትን፣ ክብርንና አክብሮትን በጠበቀ መልኩ እየተመራ ይገኛል። ሃላፊው አክለውም፦
“ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሕግ ሳይጥሱ እንዲመለሱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር እጅና ጓንት ሆነን በመስራታችን ደስተኛ ነኝ። ወደፊት መመለስ ቢፈልጉ እንኳ ፈቃድ ይዘው መምጣት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።
አያይዘውም “ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው በርካታ የውጭ ዜጎች ከእኛ ጋር ይኖራሉ። ደቡብ አፍሪካውያንም በሌሎች ሀገራት እንደሚኖሩ ስለምንረዳ ይህ ለእኛ ችግር አይደለም፤ ደቡብ አፍሪካ የሁሉም ሀገር ነች ብለን እናምናለን። ዜጎች ነገር ግን በማንኛውም ሌላ ሀገር ውስጥ ሲኖሩ ሕጋዊ ሰነድ መያዝ ግድ ይላል” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ባለቤታቸውንና ልጃቸውን ለመሸኘት የመጡ አንድ የማላዊ ዜጋ “ጉዟችን በመጀመሩ በጣም ደስተኞች ነን፤ ሴቶችና ሕፃናት ደግሞ ቅድሚያ ማግኘታቸው ተገቢ ነው” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል። ባለቤታቸው በበኩሏ ወደ ሀገሯ ለመመለስ በጉጉት ላይ መሆኗን ጠቅሳ “ለሁለት ሳምንታት ያህል ከባድ መከራ አሳልፌአለሁ፤ ዛሬ ግን ወደ ሀገሬ በመመለሴና ቤተሰቦቼን ለማየት በመታደሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን የብርድ ወራት በመሆኑ ልጄ እየታመመች ነበር። እዚህ እኛ ባዕድ በመሆናችን ወደ ሆስፒታል መሄድ አትችሉም ተብለን ነበር፤ አሁን ግን ወደ ሀገሬ ተመልሼ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ስለምችል ነፃነት ይሰማኛል” ስትል ተናግራለች።
በሌላ በኩል፣ በክሩገርስዶርፕ ከሚገኘው የሊንዴላ መመለሻ ማዕከል ወደ 980 የሚጠጉ ማላውያን የሰነድ ማጣራታቸውን ጨርሰው፣ ሐሙስ ምሽት በ14 አውቶቡሶች አማካኝነት ወደ ሀገራቸው መሸኘታቸው ታውቋል።
በያፌት ገ/ህይወት
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen









No comments yet.