⚽ ሃገሩን ወክሎ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊት፦
አባቱ ሆዜ ፔድሮ ዲያስ ወታደር፥ እናቱ አና ኢቮራ የፅዳት ሰራተኛ፥ ሁለቱ ወንድሞቹ ኳስ ተጫዋችና ሂሳብ አስተማሪ እንደነበሩ አለም አያውቅም ነበር
⚽ ከባለፈው ሰኞ በፊት፦
አባቱ የልጃቸውን ስም በ1986 የአለም ዋንጫ የተሳተፈውን የአርጀንቲናዊውን ተጫዋች ሆርጌ ቫልዳኖን ስም ተውሰው ቅድሚያ ቫልዳኖ እንዳሉት፥ የኬፕቨርዲ መንግስት ግን የውጭ ሃገር ስም በህግ ክልክል ነው ብሎ ውድቅ እንዳደረገው፥ የፖርቹጊዝ ተናጋሪ ሃገራት ስም ግን ስለሚፈቀድ በሌላኛው የ1986 የአለም ዋንጫ የብራዚል ተከላካይ ጆስማር ስም እንደተሰየመ፥ ሙሉ ስሙ ጆስማር ሆዜ ኢቮራ ዲያስ እንደሆነ አለም አያውቅም ነበር
⚽ ሰባት ኳሶችን ከማዳኑ በፊት፦
አባቱ ለግዳጅ ከሃገር ሃገር በመዞሩና እናቱ በስራ ደጅ በመዋሏ ምክንያት በአያቶቹ እጅ ማደጉን፥ አስፋልት ላይ ኳስ ሲጫወት እኩዮቹ ሲያናድዱት አያቶቹ ጋር እያለቀሰ መሄድን ስለሚያዘወትር ‘ትንሹ አያቴ’ ወይም ‘አያቴ’ የሚል ተቀራራቢ ትርጉም ያለውን ‘ቮዚኒያ’ የሚለውን ቅፅል ስም እንዳወጡለት፥ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ሆኖ የልጅነት ጊዜውን ማሰለፉን አለም አያውቀውም ነበር
⚽ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ከመሸለሙ በፊት፦
እስከ 25 አመቱ የፕሮፌሽናል ተጫዋችነት እድል አለማግኘቱን፥ አንጎላ፣ ሞልዶቫ፣ ቆጵሮስ፣ ስሎቫኪያ መጫወቱን በመጨረሻ ከፖርቹጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ቻቪስ ክለብ ለአለም ዋንጫ መመረጡን፥ በተጫዋችነት ዘመኑ አንድ ዋንጫ ብቻ ማንሳቱን፥ ሰኔ መጀመሪያ ውሉ አልቆ ክለብ አልባ መሆኑን፥ ለሃገሩ ኬፕቨርዲ ለ14 አመታት በግብ ጠባቂነት ማገልገሉን አለም አያውቅም ነበር
⚽ ከአለም ዋንጫው የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ ግን፦
ከስፔን 27 የጎል ጥቃቶች ውስጥ 7 አስገራሚ ኳሶችን ሲያመክን፥ የጨዋታው ኮከብ ሽልማትን ሲቀበል፥ አያቶቹን ከሁለት አመት በፊት ማጣቱን በካሜራ ፊት ሲናገር፥ እናቱን ለአለም ዋንጫ ለማምጣት የማስያዣ ገንዘብ በወቅቱ ባለመከፈሉ እድሉ እንዳመለጣቸው በሀዘን ታጅቦ ለሚዲያ ሲገልፅ፥ አለም በተግባሩም በንግግሩም ቮዚኒያን አወቀው፤ በ90 ደቂቃ ጨዋታ ብቻ ዝናው ናኘ፤ በአንድ ምሽት የማታ እንጀራ ወጣለት
እናም፦
500ሺህ ህዝብ ያላት ኬፕ ቨርዲ አሜሪካ በላከችው የወታደር ልጅ ቮዚኒያ ግቧን አላስደፍር ብላ ስትወጣ አለም አወቃት፤ የት የምትገኝ ሃገር ነች ተብላ በሚሊዮኖች ጎግል ተደረገች
የእናቱ የቪዛ ጉዳይ የብዙዎችን ልብ ነካ፤ የአሜሪካ ምክርቤት አባላትና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆሮ ደረሰ፤ እናቱ አና ካንዲዳ ኢቮራ ቪዛ ተመታላቸው፤ በመጨረሻ የልጃቸውን ጀብዱ ለመታደም አሜሪካ ደረሱ
50ሺህ የኢንስታግራም ተከታይ ብቻ ይዞ ለአለም ዋንጫው የመጣው ባለጓንቱ ቮዚኒያ ድልና እድል ገጥመውለት ከ14 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን አገኘ
በአንድ ምሽት ዝነኛ የሆነው ቮዞኒያ የእሱንም የቤተሰቡንም በር የሚያንኳኩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በዙ፤ እናቱ ወደ አሜሪካ ሲሄዱ የቻይና ባለሀብት ከፍተኛ ድጋፍ አደረገላቸው፤ ከታላላቅ ተቋማት የማስታወቂያ ስራልን ጥያቄም ቀረበለት፤ ክለብ አልባው ግብ ጠባቂ ከቬትናም፣ ከብራዚልና ከአውሮፓ ክለቦች የተጫወትልን ጥያቄዎችም ጎረፉለት፤ በስሙ ማሊያዎች ታተሙ፤ በሃገሩ ሀውልት እንዲቆምለት ዘመቻ ተጀመረ
አፍሪካዊቷ ኬፕ ቨርዲ ዛሬ እሁድ ለሊት 7 ሰዓት በአሜሪካ ሚያሚ ከኡራጋይ ጋር ትጫወታለች፤ የቮዚኒያ አባትና ወንድሙ ቀደም ብለው አሜሪካ ገብተዋል፤ እናቱም ደርሰዋል፤ በኳስ ማቆሚያው አመሻሽ እድሜው በ40 አመቱ ከስፔን ጋር በነበረው ጨዋታ ባሳየው ድንቅ ብቃት የማታ እንጀራ ተባርኮ የቀረበለት ቮዚኒያ ዛሬ ሜዳ ላይ ሲገባ ማነው አይባልም፤ ከየት ነው አይባልም፤ ስምና ዝናው ከፍ ብሎ ግቡን ይጠብቃል።
(ታምሩ ዓለሙ)
Source: GetuTemesgen









No comments yet.