#Ethiopia | የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ከስርቆትና ከጉዳት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርቧል።
ተቋሙ የኃይል ስርቆት ሲፈጸም ጥቆማ ለሚያደርጉ ዜጎች ከተጣለው ቅጣት ላይ የ25 በመቶ የኮሚሽን ክፍያ እንደሚፈጽም በይፋ አስታውቋል።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከውሃና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ከዓለም ባንክ ጋር በመቀናጀት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫና ትምህርታዊ ስልጠና ላይ ነው።
ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ መርሃ ግብር በዋናነት ያለመው፣ የዜና አውታሮችና ጋዜጠኞች በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይልን በቁጠባ፣ በደህንነትና ከአደጋ ነፃ በሆነ መልኩ እንዲጠቀም የማስገንዘብ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ነው።
በዕለቱ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ መገናኛ ብዙኃን መረጃ በመስጠትና በማሳወቅ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፣ በከፍተኛ ወጪ ተደራሽ የሚደረገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ህብረተሰቡ ያለብክነት እንዲጠቀም በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በተቋሙ የሽያጭ እና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይኸይስ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ ስልጠናው ደንበኞች ፍጆታቸውን እንዴት ማስላት እንደሚችሉ፣ የታሪፍ አሰራሮችን፣ የደህንነት ጥንቃቄዎችን እና ምን ዓይነት ኃይል ቆጣቢ ቁሳቁሶችን መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤ ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው።
ይህ ስልጠና የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለውና በየበጀት ዓመቱ በዕቅድ የሚከናወን ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤቶች፣ በኢንዱስትሪዎችና በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መሰጠቱን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ማህበረሰቡ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ ለማድረግም በቀጣይነት ከሚዲያ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት መታቀዱን ጠቁመዋል።
አቶ ይኸይስ አክለውም፣ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን ለመቀነስና የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ጭነት የሚበዛባቸውን የዕለት ተዕለት ሰዓታት በማስወገድ፣ የኃይል ጫና የሌለባቸውን ሰዓታት በተለይም ከሌሊቱ አራት ሰዓት እስከ ጠዋት ሶስት ሰዓት ያለውን ጊዜ እንዲጠቀሙ መክረዋል።
በተጨማሪም ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ኃይል የማይበክሉና ውጤታማ የሆኑ የኤሌክትሪክ እቃዎችንና ማሽነሪዎችን መርጦ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማርኬቲንግ፣ ሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ደንድር እና የተቋሙ የኮሙዮኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር በበኩላቸው፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ ማድረግ ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት የሥራ ኃላፊዎቹ፣ በደንበኞች እና በአገልግሎት ሰጪው ተቋም መካከል ጠንካራና አስተማማኝ ድልድይ መገንባት የመረጃ ፍሰቱን ጤናማ፣ ግልጽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አስምረውበታል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.