“አሉ” ቴአትር መታየት ጀመረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የአዲስ አበባ ከተማ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ”ትንሹ አለ ተባለ” በትልቁ ሀገር ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በሚገባ የሚያሳይ “አሉ” የተሰኘ አዲስ የትርጉም ቴአትር በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ማሳየት ጀመረ።

የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ዘገየ እንደገለጹት “ስፕሬዲንግ ዘ ኒውስ” በአጉስታ ግሪጎሪ የተጻፈ የአይሪሽ ተውኔት ሲሆን በአንጋፋው ጸሐፌ ተውኔት ተፈሪ አለሙ ወደ አማርኛ ተመልሶ በሀይለገብርኤል ረዳት አዘጋጅነት ማለፊያ ሆኖ ለመድረክ በቅቷል።

በተጨማሪም ”አሉ” ቴአትር በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ጠቃሚና ማኅበረሰብ ተኮር መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ታስቦ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል ።

ቴአትሩ ማኅበረሰቡ መረጃዎችን በኃላፊነትና በምክንያታዊነት እንዲመረምር ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በአሉባልታ ፈንታ እንደ ንጋት የጠራውን እውነት ብቻ ይዞ በወንድማማችነት ስሜት አብሮ መኖር እንደሚሻል ይነግረናል።

​ከአየርላንድ ኤምባሲ ጋር በጋራ ፕሮዲውስ የተደረገው ይህ ባለ አንድ ገቢር ቴአትር አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎችን ያቀናጀ ሲሆን እንደ ፍቃዱ ከበደ ፣ቅድስት ኃይለ ሥላሴና ዮዲትን የመሰሉ ድንቅ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

ሁለት ወራት በሚሆን የልምምድ ጊዜ ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ይህ ተውኔት ይዘቱ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያዊ የኑሮ ውቅርና ባህል ጋር እንዲስማማ ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ለተመልካች የተለየ ስሜት እንደሚፈጥር በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል። ”አሉ” ዘወትር ረቡዕ በ11:30 በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለሁሉም እንደሚቀርብም ሰምተናል።

​አቶ ፍጹም ወቅታዊውን የቲያትር ቤቶች የተመልካች ድርቀትና የአዳራሽ ኪራይ ዋጋ መናርን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ደረጃ ላይ ባለመሆኑ አሰራሮችን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ማሰናሰል የግድ ይላል ብለዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ አስተዳደሩ ከኢንተርፕራይዞች ጋር በአጋርነት የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ በቀጣይም ቴአትርን ከአዳራሽ በማውጣት በጎዳናዎች፣ በአምፊ ቴአትር ክፍት ቦታዎች ላይ ማሳየት እንዲሁም እንደ ቴሌብር ባሉ ዲጂታል መድረኮች ትኬቶችን ተደራሽ በማድረግ የጥበብ ዘርፉን ማዘመን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: