#FastMereja I ቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ በጤና አገልግሎት ጥራትና በታካሚዎች ደህንነት ዙሪያ ባሳየው የላቀ ብቃት፣ የጆይንት ኮሚሽን ኢንተርናሽናል (JCI) የወርቅ ደረጃ ዕውቅናን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘቱን አስታወቀ።
በየዓመቱ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ውጭ አገር ለሕክምና በመጓዛቸው ሳቢያ የምታጣውን ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ታስቦ የተቋቋመው ይህ ሜዲካል ፕላዛ፣ አንደኛ ዓመት ክብረ በዓሉን እና የዕውቅና ማብሰሪያ መርሐግብሩን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በተገኙበት አክብሯል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በጤናው ዘርፍ የአገልግሎት ጥራት፣ ፍትሐዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። መንግሥት እንደ ቤተሳይዳ ያሉ አገልግሎትን የሚያዘምኑ፣ አቅም ያላቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ የግል የጤና ተቋማት የሚያደርጉትን የማስፋፊያ ሥራዎች በቅርበት የመደገፍና የማገዝ ቃል ኪዳን እንዳለውም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
ተቋሙ ይህንን ታዋቂ የዓለም አቀፍ ምስክር ወረቀት ለማግኘት የታካሚዎች መብትና ደህንነትን፣ ጥራቱን የጠበቀ የመድኃኒት አስተዳደርን እንዲሁም አስተማማኝ የኢንፌክሽን ቁጥጥርን ጨምሮ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጠንከር ያሉ መስፈርቶችን ማለፉ በዕለቱ ተገልጿል። ይህ የጥራት ዕውቅና ደረጃውን ጠብቆ ለማስቀጠል ሲባል በየሦስት ዓመቱ በሚደረግ ጥብቅ ድጋሚ ምርመራ የሚታደስ ይሆናል።
የቤተሳይዳ አሜሪካን ፕላዛ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አየለ ተሾመ በበኩላቸው፣ ዕውቅናው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ ልቀት ካርታ ላይ የሚያስቀምጣት መሆኑን ገልጸው፣ አገራችን በዓለም ላይ እጅግ የተከበሩ መመዘኛዎችን የሚያሟሉ ተቋማትን መገንባትና ማንቀሳቀስ እንደምትችል ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ይህ ሜዲካል ፕላዛ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዙና በድምፅ መታዘዝ የሚችሉ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን በሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን፣ ይህም ያለ ኦፕሬሽን የልብ፣ የአንጎልና የደም ሥር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ተጠቁሟል። ተቋሙ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋፋት ዘመናዊ የካንሰር ሕክምና እና የሰው ሠራሽ ማፅነስ (IVF) ማዕከላትን በማቋቋም ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።



Source: FastMereja









No comments yet.