ሕግ፣ አፈጻጸም፣ ክፍተት እና መፍትሄ
በኢትዮጵያ ህግ ማእቀፍ እና ተጨባጭ የህግ አፈጻጸም
በጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው 0929101037
የዚህ ጽሁፍ መነሻ ሀሳብ
#Ethiopia | ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ወጥነት ያለው የጉዳዮች ክስ አቀራረብ አስመልክቶ አንዳንድ ጉዳይ ጉዳዩ በተከሰተበት ወይም ለጉዳዩ መነሻ በሆነበት ላስቻለው ፍርድ ቤት ሲከፈቱ አንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ የጉዳዩ መነሻ ከሆነበት ስፍራ ይልቅ እንደዚህ አይነት ጉዳይ በልዩ ችሎት በዚህ ክፍለከተማ ባለው በተቋቋመው ምድብ ችሎት እንጂ ይህ ፍርድ ቤት ይህንን ጉዳይ ሊመለከት አይችልም ስለዚህ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በልዩ ሁኔታ በተቋቋመበት ሄደህ መክፈት እንጂ እዚህ ሊከፈት አይችልም በሚል የጉዳዩ መነሻ የተከሰተበት ስፍራ የግዛት ስልጣን ያለው ተመሳሳይ ፍርድ ቤት ማየት አይችልም ተብሎ ለምሳሌ ከፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ ችሎት የጉዳዩ መንስኤ የሆነው ጉዳይ የማንንቀሳቀስ ንብረትም ሊሆን ይችላል እዚህ አቃቂ ቃሊቲ ያለው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከህግ አንጻር የማየት ስልጣን እያለው የልደታ ወይም የአራዳ ምድብ ችሎት ነው የሚያየው ተብሎ የፍትህን ተደራሽነትን ዋጋ ሊያሳጣ በሚችል ደረጃ የፍተሀብሔር ስነስረአት ህግ አላማን ወደ ጎን በመተው ላልተፈለገ ወጪ ፣እንግልት ፣ ኪሳራ፣ ለኢፍትሀዊ እና ለዘገየ ፍትህ የምንዳረግ መሆኑን መገንዘቤ የዚህ ጹሁፍ መነሻዬ ነው ሲሆን የሚያጠነጥነው የፍተሀብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ ይሆናል።
መግቢያ
የዚህ ጹሁፍ አላማ “በአዲስአበባ ውስጥ የሚገኙ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የግዛት ስልጣናቸው የሚወሰነው በፍርድ ቤቶች አመራር፥ ፥ አስተዳደራዊነት ወይንስ በፍተሀብሔር ወይም በወንጀል አግባብ ባለው የህግ ስልጣን መሠረት?” የሚለውን የተዛባ አሰራር ህጋዊ አስተያየት በመስጠት ሊጠራ የሚገባው ጉዳይ በመሆኑ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ነገር የፍተሀብሔር እና ወንጀለኛ ስነስረአት አላማው ነው። የእነዚህ ስነስረአት አላማቸው ምንድነው? ተደራሽነት፣ፍትህ፣ወጪ፣ጊዜ፣የተፋጠነ ፍትህ ከመስጠት አንጻር ግባቸው ምንድነው”የሚለው ጉዳይን በማጤን ጭምር በዚህ ጹሁፍ የምንመለከተው ነው። ይህ ጹሁፍ የራሴ የግል ሀሳብ ተደርጎ ቢወሰድም ከዚህ አንጻር ግርታን የሚፈጥሩ ሀሳቦችን በውይይት፣በጥናት የተሻለውን ለመውሰድ መነቃቃትንና አግባብነት አንጻር የራሱ የሆነ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ በማሰብ ይህንን ጹሁፍ ለንባብ አብቅቻለው።
1. የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር አወቃቀር ከፍርድ ቤቶች ተደራሽነት አንጻር….
አዲስአበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስትሆን በአስራ አንድ ክፍለከተሞች የተከፈለች ናት። ህዝቦቿ በእያንዳንዱ ክ/ከተማ ብዛት ያላቸው፣ ትላልቅ ኃላፊነት የተሰጣቸው የተለያየ የመንግስት አስተዳደር አካላት ፣ የአገልግሎት ተቋማት፣ የንግድ ትስስሮች ያሉባት የፌደራል መንግስት እና የአፍሪካ መዲና መቀመጫ ናት። ይህ እንደ መሆኑ መጠን የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ስልጣንን ፣ የአገልግሎት ኃላፊነትን፣ በህግ የተሰጠ ስልጣን፣መብት፣ግዴታ የአዳስአበባ ከተማ አስተዳደር ለክፍለ ከተሞች የሰጠው የስልጣን ክፍፍል ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ ባሻግር በክፍለከተሞች የሚመለከታቸው ቢሮዎች ፣ የንግድ ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ተቋማት ተደራጅተው ይገኛል። ይህ እንደ መሆኑ መጠን ፍርድ ቤቶቻችን ሲደራጁ ሲዋቀሩ ከእነዚህ አስተዳደራዊ መዋቀር ጋር በመናበብ ለዜጎች ተደራሽ ሊሆኑ ያስፈልጋል።
2. የፍርድ ቤት የግዛት ስልጣን በኢትዮጵያ ፍተሀብሔር ስነስረአት ህግ/local jurisdiction/ እና በወንጀል ስነስረአት
የፍርድ ቤት ግዛት ስልጣን አስመልክቶ በፍተሀብሔር ዋናው አላማው በግዛቱ ለሚኖሩ ሰወች በመቅረብ ተደራሽነትን ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን ተከራካሪ ወገኖች ያሉበት አከባቢ፣የክርክሩ ምክንያት የሆነው ነገር፣የማይንቀሳቀስ ንብረት ለክርክሩ መነሻ ሲሆን ፣ የክርክሩ መነሻ ውል ሲሆን ፣ ከሳሽ መንግስትን ከሳሽ ሲሆን፣ የተከሳሽ አድራሻ ባለበት ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባው በአጠቃላይ በፍተሀብሔር ስነስረአት ህግ ቁጥር ከ19 እስከ ድረስ ባለው የግዛት ስልጣን አስመልክቶ ተከራካሪው ወይም የክርክሩ መነሻ ባለበት ባለው አቅራቢ ፍርድ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ ይደነግጋል። ለዚህም አላማው ወጪ ለመቆጠብ፣የተከራካሪ ወገኖችን እንግልት ኪሳራ ለማስቀረት፣ጉዳዮቹ ቀልጣፋ በመሆን አጠር ባለ ጊዜ ፍትሀዊ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል። የወንጀል ጉዳይም በተመለከተ ጉዳዩ ለተፈጸመበት ስፍራ ላለው ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ነው።
3. አዲስአበባ ላይ የሚገኙ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ስልጣን ላይ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የግዛት ስልጣንን ተግባራዊ ያለማድረግ ችግር….
በየክፍለከተማው ያሉ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በፍርድ ቤት አስተዳደር ምክንያት ስልጣናቸው ተመሳሳይ ሲሆን በጉዳዮች አይነት ለተለዩ ክፍለከተማ ፍርድ ቤቶች የተለዩ ጉዳዮችን ተለይቶ የሚሰጥ ሲሆን ይህ የፍትሀብሄር ስነስረአትን ህግ አላማ ከግምት ውስጥ ያላስገባና የህገመንግስትን ፍትህ የማግኘት ፣ ዜጎች
በራሳቸው አስተዳደር መዋቀራዊ መንግስት የዳኝነት አገልግሎት እንዳያገኝ የሚያደረግ ነው። ኢፍትሃዊነቱን ለማንሳት ያህል፣በእኩል የመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ስር የሚገኙ ህዝቦች ወይም ዜጎችን መሠረታዊና በመንግስት እንኳን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገደብ የማይችል ህገመንግስታዊ የእኩልነት መብት ጋር የሚቃረን በየክፍለከተማው ተመሳሳይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚያዩበትን የጉዳዮች መጠን በመለያየት የአከባቢው ማህበረሰብ አቅራቢያ በሚገኘው ፍርድ ቤት አገልግሎት እያጡ በሌላ ክፍለከተማ ባሉ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ ለተጨማሪ ወጪና ኪሳራ ከመዳረጋቸውም በላይ ዳኞች የሰነድ እና ሌሎች ማስረጃዎችን ከሌላ ክ/ከተማ ለማስመጣት እና ህጎቻቸውን ተፈጻሚ ለማድረግ ተግዳሮት የሚፈጥርና ለዘገየ ፍትህ ምክንያት የሚሆን ነው።
ምሳሌ አንድ :- በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት ያለው አንድ ክ/ከተማ ነው። በሌሎች ክፍለ ከተማ እነዚህ የፍርድ ቤት አገልግሎቶች ባለመኖራቸው ባለጉዳዮች ከየትኛውም የአዲስአበባ ቦታ በመመላለስ ለተለያየ እንግልት እና ለዘገየ ፍትህ የሚዳርግ ሲሆን በሌሎች ክ/ከተማ ያሉትን ሰወች የእኩልነት መብት መርህ ጋር የሚጣረስ ነው።
ምሳሌ ሁለት:- የመንግስት አስተዳደር ተከሳሽ በሚሆንበት ጊዜ
ጉዳዩ ልደታ ያለው መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ብቻ እንዲታይ ማደረጉ በተመሳሳይ በህጉ መሠረት ሌሎች ክፍለከተማ ያሉት የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤቶች እንዲያዩ የተሰጣቸውን ስልጣን ያለ ህግ ልደታ የሚገኘው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ብቻ ማድረግ የፍትህ ተደራሽነት እኛ የተቀላጠፈ ፍትህን ከግምት ውስጥ የማያስገባ ለዘገየ ፍትህ በር የሚከፍት ነው።
ምሳሌ:-ሦስት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በየክፍለከተማው ለማድረግ የበጀት ማነስ ወይም ሌላ ምክንያት ቢኖረውም በየክፍለከተማው ያሉት ውስን ፍርድ ቤቶች የሚመጡትን ጉዳዮች ስልጣኑ እስከሆነ ድረስ የግዛት ስልጣን እስካለው ድረስ ፤ በፍርድ ቤት አመራር አቅጣጫ ምክንያት ከህግ የመነጨ የፍርድ ቤት ስልጣንን ወደ ጎን በመተው አቤቱታዎችን ለመቀበል መለያየት ተገቢነት የለሌው ነው። ለዚህም ለመጥቀስ ያህል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቲ አቃቂ ቃሊቲ ምድብ ችሎት በፍተሀብሔር ቀጥታ ሳይሆን በይግባኝ ብቻ መመልከቱ በቀጥታ ክስ የማየት ስልጣኑን በመከልከል ይግባኝ ጉዳይ ብቻ እንዲመለከት መደረጉ ፍትሀዊ እና የእኩልነት አገልግሎት መርህን ያላከበረ ነው።
4. የጸሃፊው የህግ አስተያየት እና ምክር
ከፍርድ ቤቶች ስልጣን መካከል አንዱ የግዛት ስልጣን መሆኑ ይታወቃል። ይህም የግዛት ስልጣን በፍተሀብሔር ስነስረአት ህግ ላይ ተደንግጎ የተቀመጠን በፍርድ ቤት አመራር አቅጣጫ ወይም መመሪያ ሊቀየር የማይገባ እና የህግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። በመሆኑም በሁሉም ክፍለከተማ ያሉትን ዜጎች ካልተገባ ወጪ ለመታደግ ፣ የዜጎች እኩልነት፣የተፋጠነ አገልግሎትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በፍትሃብሔር ስነስርዓት ህጉ ላይ የተቀመጠውን የግዛት ስልጣን በተመለከተ የተደነገጉ ህጎችን ለማረጋገጥ በሁሉም ክፍለከተማ የሚገኙ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መጀመሪያ ፣ ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ያለቸው እስከሆነ ድረስ ማየት ይገባቸዋል እንጂ የአቃቂ ቃሊቲ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወይም ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ይህን ጉዳይ ለማየት ስልጣን የለውም በማለት የልደታ፣ ወይም የአራዳ ፌደራል መጀመሪያ/ከፍተኛ ደረጃ ምድብ ችሎት ነው ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ያለው በማለት የሚደረገው ጉዳዮችን በክፍለከተሞች በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን ያለ ህግ ስልጣናቸውን መለያየት ህገወጥ በመሆኑ ሊስተካከል ያስፈልጋል።
ማጣቀሻዎች/References/
1. የኢትዮጵያ ፍተሀብሔር ስነስረአት ህግ
2. የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013
3. የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር
https://t.me/Fantahunlawyer
tiktok.com/@fantahun214
https://www.facebook.com/share/1Hhfy6ZDjf/
Source: GetuTemesgen









No comments yet.