#Ethiopia | በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት አካባቢ ልዩ ቦታው ሌማት ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ የግል ተበዳይ ከመኖሪያ ቤቱ በመውሰድ የእገታ ወንጀል የፈጸሙ ሦስት ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ሰለሞን ቢራራ፣ እሱባለው አግማሴ እና ሳንቾ ጌታቸው የተባሉ ሲሆን፣ ወደ ተበዳዩ መኖሪያ ቤት በመሄድ የአለቃችንን ልጅ ወደ ውጭ ሀገር ልከሃል በሚል 500 ሺህ ብር ተቀብለሃል፣ ስለዚህ በወንጀል ትፈለጋለህ የሚል ሀሰተኛ ምክንያት አቅርበዋል።
በመቀጠልም የሀሰት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የመከላከያ መታወቂያዎችን በማሳየት፣ ወደ ጦር ኃይሎች አለቃችን ጋር እንወስድሃለን በማለት በተሽከርካሪ አግተውት ተጉዘዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የተወሰነ ርቀት ከተጓዙ በኋላ አቅጣጫቸውን በመቀየር ወደ ቢሾፍቱ ፈጣን መንገድ ካቀኑ በኋላ፣ ከአለቃችን ጋር ካደረስንህ የከበደ ቅጣት ስለሚጠብቅህ በሞባይል ባንክ ገንዘብ ገቢ አድርግልንና እንልቀቅህ ሲሉ ጠይቀውታል። የግል ተበዳዩ የፈጸምኩት ወንጀል ስለሌለ ወደ ህግ ውሰዱኝ በማለቱ ድብደባ ፈጽመውበታል።
በመጨረሻም 600 ሺህ ብር በሞባይል ባንኪንግ እንዲላክላቸው ካደረጉ በኋላ፣ ከተሽከርካሪው አውርደውት መሰወራቸውን የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የላም በረት አካባቢ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኢዮብ ተከተል ገልጸዋል።
ፖሊስ ባደረገው ክትትልም ከቢሾፍቱ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገ ትብብር ም/መቶ አለቃ ሰለሞን ቢራራን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
በተከናወነው የምርመራ ማስፋፋት ስራ ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊት የከዳውን ም/መቶ አለቃ እሱባለው አግማሴን ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መያዝ ተችሏል።
በተጨማሪም ሀብት ያላቸውን ሰዎች መረጃ በማጠራቀም ለወንጀል አድራጊዎች ጥቆማ ሲሰጥ የነበረውን ሳንቾ ጌታቸው የተባለ ተጠርጣሪ በላምበረት መናኸሪያ አካባቢ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የምርመራ መዝገቡ ያመለክታል።
ከተወሰደው ገንዘብ ውስጥ 135 ሺህ ብር እና በዚሁ ገንዘብ የተገዛ 70 ሺህ ብር ግምት ያለው ላፕቶፕ በኤግዚቢትነት የተያዘ ሲሆን፣ ቀሪውን ገንዘብ ለማስመለስ እና ያልተያዘውን አንድ ተጨማሪ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትል ስራው ቀጥሏል።
ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውስጥ አምስት ተመሳሳይ የእገታ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ለፖሊስ ቃል የሰጡ ሲሆን፣ ጉዳዩ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ጋር በመቀናጀት በስፋት እየተመረመረ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ህብረተሰቡ የጸጥታ አካል ነን፣ በህግ ትፈለጋላችሁ በሚሉ ሀሰተኛ ቃላት በመጠቀም አታለው ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት በመኖራቸው፣ እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በፍጥነት በአቅራቢያ ለሚገኝ የጸጥታ ተቋም ጥቆማ መስጠት እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።
#EthiopianPolice #CrimeNews #YekaSubCity #Bishoftu #AddisAbabaPolice #SecurityUpdate
#getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen









No comments yet.