የአዲስ አበበ ገቢዎች ቢሮ በተሽከርካሪ ኮሚሽንና አገናኝነት ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሻጮችን ተሽከርካሪ በድርጅታቸው ቅጥር ግቢ አከማችተው መሸጥ በህግ የተከለከለ መሆኑን በመግለጽ፣ በግቢያቸው የሚገኙ መኪኖችን በአስቸኳይ እንዲያነሱ ጥብቅ ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።
ቢሮዉ ያስተላለፈውን ጥብቅ መመሪያ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አብዛኞቹ የኮሚሽን ነጋዴዎች ተሽከርካሪዎችን ከግቢያቸው እያወጡ ይገኛሉ። ካፒታል የደረሰዉ እንደሚያመለክተው ካለፉት ሁለት ቀናት ወዲህ በታክስ ባለስልጣኑ የተላለፈው ይህ መመሪያ በተግባር መሬት ማውረድ ተጀምሯል።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ነጋዴዎች በበኩላቸው ውሳኔው አግባብ እንዳልሆነና በስራቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ቢገልጹም፣ የተላለፈውን መመሪያ በማከበር ተሽከርካሪዎቹን ከግቢያቸው በማስወጣት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የታክስ ባለስልጣኑ ከቀናት በፊት ይፋ ባደረገው መመሪያ መሰረት፣ በፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ማንኛውም ግብር ከፋይ ባገኘው ገቢ መጠን ልክ ህጋዊ ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት። በተጨማሪም በተሻሻለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2017 ህግ መሰረት “የአቅርቦት ቦታ” የሚባለው የእቃ ወይም አገልግሎት አቅራቢው የንግድ መደብር፣ መጋዘን ወይም የእቃ ማሳያ ቦታ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል።
ይህን ተከትሎ ቢሮዉ በተሽከርካሪ ንግድና አስመጪነት ዘርፍ የተሰማሩ ህጋዊ ነጋዴዎች ብቻ ናቸው የራሳቸውን ንግድ በሚያከናውኑበት ህጋዊ ቦታ ላይ ሽያጭ ማከናወን የሚችሉት በማለት አስጠንቅቋል።
በተቃራኒው በኮሚሽን ወይም በአገናኝነት የተሰማሩ ወገኖች ገዥና ሻጭን በማገናኘት የሚገባቸውን ክፍያ መቀበል ሲገባቸው፣ የሻጭን መኪና በድርጅታቸው ግቢ አከማችተው መሸጣቸው ያለ ንግድ ፈቃድ መስራትና የመንግስትን ታክስ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ማገዝ እንደሆነ ባለስልጣኑ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ የኮሚሽን ድርጅቶች ማስጠንቀቂያዉ በደረሳቸው ቀናት ውስጥ በግቢያቸው ውስጥ የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን በሙሉ ማስወጣትና ማንሳት እንዳለባታቸዉ ቢሮዉ አመልክቷል።
ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ባለስልጣኑ በታክስ አስተዳደር አዋጅ መሰረት የንግድ ድርጅቱን የማሸግና ሌሎች ህጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን አስታውቋል።
Via capital
Source: Yeneta Tube









No comments yet.