#የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች… በደም የተጻፈ ታሪክ

- Advertisement -
Sidebar AD

በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች ማለትም ከራሷ ከሮምና ከአንጾኪያ ነበር፡፡ የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ፣ ገላውዴዎስ፣ ፊቅጦር፣ አውሳብዮስና ሌሎቹም፤ ሴቶቹ ቅዱሳቱ ማርታ፣ ሶፍያ፣ ኢራኢ፣ ታኡክልያና ሌሎቹም ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ፣ ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ሕይወቱ አለፈ:: የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች፡፡ ቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ሌሎቹ ዙፋኑን በቀላሉ መያዝ ቢችሉም እነሱ ግን ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ፡፡

በዚህ መሀል ከንጉሡ ልጆች 2ቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አግሪዻዳ የሚባል ጉልበተኛ ሰው ማንም በሌለበት ስሙን ዲዮቅልጢያኖስ ብላ አንግሣ ጠበቀቻቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም፡፡ የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው፡፡ ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው፡፡ ዓለምም በእነዚህ ጨካኞችና በሚሊየን በሚቆጠሩ ሠራዊታቸው እጅ ወደቀች፡፡ የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ቅዱስ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ “ይህ ዓለም ከነክብሩ ጠፊ ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ” አላቸው::

ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ በደስታ ምድራዊ ክብራቸውን ትተው በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ ይጸልዩ ጀመር:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው:: ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ:: አጵሎን፣ አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቁሞ አብያተ ክርስቲያናት ይዘጉ አብያተ ጣዖታት ይከፈቱ” ብሎ አሳወጀ:: በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ:: ምድር በደም ታጠበች፣ ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ፣ ሃይማኖታቸውን ለማስካድ ስቃያቸው በዛ፣ በእሳት ተቃጠሉ፣ ታሠሩ፣ ተሰደዱ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም፡፡ ይልቁኑ እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው እንደ ብዕር አጥንታቸው ቆዳቸው እንደ ብራና ሆኖ ነው እንጂ፡፡

ቅዱሱ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ሰማዕታትን “ተጋዳዮች፣ የሚያበሩ ኮከቦች፣ የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች” ይላቸዋል:: እነሱ እየቀለጡ አብርተዋልና፡፡ ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም “ዘመነ ሰማዕታት” የሚባለው ከ150 እስከ 312 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን ነው፡፡ በተለይ ግን ከ270ዎቹ እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል፡፡ የሰማዕታት የጽናታቸው ምሥጢር ቃለ ወንጌል የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ከነዚህ ሰማዕታት አንዱ የኑማርያኖስ ባለሟል የነበረው ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘሮም የካቲት 28 ሰማዕት የሆነበት በዓለ እረፍቱ ነው፡፡ የቅዱሳን በረከት እንዲያድርብን ገዳማትን እንርዳ፡፡

ገዳማዊያን በዓለም ላለነው ለኛና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ለሀገራችንም ይጸልያሉ፡፡ ገዳማቸውን በመርዳት፣ በዓታቸውን በማጽናት ከበረከታቸው እንሳተፍ፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1