#Ethiopia | ለግማሽ ዓመት ያህል በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር የሰነበተው የዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነ ታላቅ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ፍጻሜውን አግኝቷል።
በዕለቱ የክብር እንግዳ በመሆን የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ባንኩ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እና የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ላበረከተው ጉልህ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ገዥው አክለውም ባንኩ የተጀመረውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም በመደገፍ በመጪው የለውጥ ምዕራፍ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው የባንኩ የ30 ዓመታት የስኬት ጉዞ የደንበኞች፣ የባለድርሻ አካላትና የሠራተኞች የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ ወደፊትም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ለሀገር እድገት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ባንኩ ከጥር 2018 ዓ.ም ጀምሮ የ30ኛ ዓመት ኤክስፖ፣ የኢኖቬሽን ወር እና የሴቶች አቅም ማጎልበቻ መርኃ ግብሮችን ጨምሮ በርካታ ዝግጅቶችን ሲያካሂድ መቆየቱ ተጠቅሷል።
በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባንኩ ለአሁኑ የስኬት ደረጃው እንዲበቃ ስያሜ ከመስጠት ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉት ለክቡር ሸኽ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲን ልዩ የዕውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
ከተገቢው ክብር ጋር ለ11 የባንኩ መስራቾች፣ ለቀድሞ የቦርድ አመራሮች፣ ለቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ለአጋር ተቋማት፣ ለረጅም ዘመን ደንበኞች እና የረጅም ጊዜ አገልግሎት ላላቸው ሠራተኞችም ዕውቅና ተሰጥቷል።
የማህበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩ አካል አድርጎም ባንኩ በአዕምሮ እድገት ውስንነት ላላቸው ወገኖች ድጋፍ ለሚያደርገው ለዲቦራ ፋውንዴሽን የ30 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ስጦታ አበርክቷል።
በሌላ በኩል በዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያ በተካሄደው የዕድል ጨዋታ አሸናፊ ለሆነው ደንበኛ የዘመናዊ ቢዋይዲ ሴጉል የኤሌክትሪክ መኪና ሽልማት ተላልፏል።
በዚህ ታላቅ መርሃ ግብር ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ኢዮብ ተካልኝን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የሀገር መሪዎች፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
#DashenBank #Banking #EthiopianEconomy #Finance #DeborahFoundation #BYD #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa


Source: GetuTemesgen









No comments yet.