ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር እና ህጋዊ ዉጤቱ

- Advertisement -
Sidebar AD

⚖️

​በጠበቃ እና የህግ አማካሪ አለምሰገድ አብርሃም
📞 0910 211365 / 0931775959

​መግቢያ
#Ethiopia | የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ ጋብቻ የሚፈጸምባቸውን መንገዶች (በክብር መዝገብ ሹም፣ በሃይማኖት እና በባህል) ይዘረዝራል። ከነዚህ ውጪ ግን በተለምዶ ብዙዎች የሚኖሩበት “ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር” (Irregular Union) በህግ እንዴት ይታያል? ንብረት እና እዳስ እንዴት ይዳኛል?

​1️⃣ የ”Irregular Union” ምንነት

በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 98 መሰረት አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት መደበኛ ጋብቻ ሳይፈፅሙ ነገር ግን “በትዳር መልክ” አብረው ሲኖሩ ማለት ነው።

ይህ ማለት፡-
​ወንዱና ሴቷ ልክ እንደ ባልና ሚስት አብረው መኖር አለባቸው።
​በመካከላቸው የፀና ሌላ ህጋዊ ጋብቻ መኖር የለበትም።

​2️⃣ ህጉ ለምን ጥበቃ አደረገለት?

ምንም እንኳን ይህ ግንኙነት መደበኛውን የጋብቻ ክብር የሚቀንስ ቢመስልም፤ ህጉ ጥበቃ ያደረገለት፡-
​በዚህ ግንኙነት ውስጥ የሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት፣
​በተለይም በዚህ ግንኙነት ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶች በመሆናቸው መብታቸውን ለማስከበር ነው።

​3️⃣ የዚህ ግንኙነት ህጋዊ ውጤቶች

​ሀ) ዝምድናን በተመለከተ፡-

ልክ እንደ መደበኛ ጋብቻ ሁሉ፤ በዚህ ግንኙነት ውስጥም በወንዱ እና በሴቷ የስጋ ዘመዶች መካከል ጋብቻ መፈፀም የተከለከለ ነው። (አንቀፅ 100(2))

​ለ) ንብረትን በተመለከተ (ወሳኝ ነጥብ!)፡-

​የ3 ዓመት ህግ፡- ወንዱ እና ሴቷ ከ3 ዓመት ላላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያፈሩት ንብረት የጋራ ንብረት እንደሆነ በህግ ይገመታል። (አንቀፅ 102(2))
​ይህንን ግምት ማስተባበል የሚፈልግ ወገን ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል።

​ከ3 ዓመት በታች ከሆነ፡- የጋራ ንብረት የሚባለው ንብረቱ በሁለቱም ገንዘብ ተዋጥቶ መገዛቱ ከተረጋገጠ ብቻ ነው።

​ሐ) እዳን በተመለከተ፡-

​ለጋራ ኑሮ ወይም ለልጆች ማሳደጊያ የተገባ ማንኛውም እዳ የጋራ እዳ ነው።
​ለእዳ አከፋፈል የ3 ዓመት ጊዜ መጠበቅ አያስፈልግም። ግንኙነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለኑሮ የተገባ እዳን የመክፈል ግዴታ አለባቸው።

​4️⃣ ማስረጃ እና ማረጋገጫ

ይህ ግንኙነት መኖሩን ለማረጋገጥ የፅሁፍ ማስረጃ የግድ አይደለም። ዋናው ነገር፡-
​ቤተዘመድ እና ማህበረሰቡ እንደ ባልና ሚስት የተቀበሏቸው መሆኑ፣
​በውጭ ሲታዩ እንደ ተጋቡ ሰዎች ሆነው መገኘታቸው በቂ ማስረጃ ነው።

​5️⃣ ግንኙነቱን ስለማቋረጥ

ይህ ግንኙነት ለመቋረጥ እንደ ፍቺ አይነት መደበኛ የፍርድ ቤት ክርክር (ስርዓት) የግድ አይፈልግም። በማንኛውም ጊዜ ሊቋረጥ ይችላል፤ ነገር ግን የንብረት እና የልጆች ጉዳይ በህጉ መሰረት ይዳኛል።

​💡 ምክር፡ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር በቆይታ ሂደት ውስጥ የጋራ ንብረት እና የጋራ እዳን ስለሚያስከትል፤ ጥንዶች ህጋዊ ውጤቱን አስቀድመው ተረድተው መኖር መልካም ነው።

​✍️ አቶ አለምሰገድ አብርሃም (ጠበቃ እና የህግ አማካሪ)
📍 ለተጨማሪ የህግ ምክር፡ 0910 211365 / 0931775959


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1