ቅጠል ተራን ወደ ውብ መኖሪያ ሥፍራ!

- Advertisement -
Sidebar AD

ለመኖር እጅግ ምቹ ያልሆነ፤ ለሰው ልጅ ክብር በማይመጥን፤ በጣም የቆሸሸ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ እንዲሁም ከተማ እምብርት ላይ ሆነው በተተበተበ ለአደጋ አጋላጭ የሆነ የኤሌክትሪክ መስመር ብሎም በኩራዝና በሻማ የሚጠቀሙ ነዋሪዎች ይኖሩበት የነበረውን የቅጠል ተራ ሰፈርን፣ ወደ ውብ መኖሪያ አካባቢነት ለመቀየር ዛሬ ባለ 8 ወለል የሆኑ ብዛታቸው 9 ህንጻዎች ከ500 በላይ ቤቶችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠናል።

ይህ ፕሮጀክት አካባቢው መንገድ ያልነበረው፣ እንደ ሸረሪት ድር የተጠላለፉ ገመዶች የበዙበት፣ ነዋሪዎች በድህነት ምክንያት ኑሯቸውን ለመደጎም ቤታቸው ውስጥ ቆጥ ሰርተው አልጋ የሚያከራዩበትና ሰዎች ላይ ቆልፈው በሚሄዱበት ጊዜ በሚፈጠር የእሳት አደጋ የሰዎች ህይወት የሚጠፋበት፣ ንብረት የሚወድምበት፣ እጅግ ብዙ ገመናዎችን የያዘ አስከፊ የሰው ህይወትን የሚቀይር ፕሮጀክት ነው።

አካባቢው የከተማ እምብርት ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን በብዙዎቹ የገጠር አካባቢዎች እንኳን የቀረውን ሻማ እና ኩራዝ የሚጠቀም ነዋሪ ያለበት አካባቢ ነው።

መርካቶ አካባቢ ብዙ “ተራ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው – ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ፣ ቦንብ ተራ … ጠጋ ብለን ስናያቸው የነዋሪዎቻችን የአኗኗር ሁኔታ እና ገፅታውን የሚያሳዩ ናቸው። እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ደጋግመን በማውራት ነዋሪው ሆድ እንዲብሰው ማድረግ ሳይሆን፣ መፍትሄው ሰርተን ህይወቱ እንዲቀየር እና ለሰው ልጆች የሚመጥን የክብር ኑሮ እንዲኖር እዚያው የመኖሪያ ቤት እና የንግድ ቦታዎች እንዲያገኝ ማድረግ ነው ።

በከተማችን ዋነኛ የስራዎቻችንን ማዕከል ሰው ተኮር ስራዎች አድርገን እየሰራን እንገኛለን ።
በቅጠል ተራ ያስጀመርነው የቤት ግንባታ 10ሺህ ካሬ ላይ ያረፈ፤ ተገንብቶ ሲጠናቀቅም ከ20,000 በላይ ሰዎችን ንፁህ፤ ለሰው ክብር የሚመጥን ዘመናዊ አኗኗር ያለው መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጅክት ነው ።

ፕሮጀክቱ ልጆች ቦርቀው እንዲያድጉ የስፖርት ሜዳ እንዲሁም የንግድ ሱቆች እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውለት በጥራት እና በፍጥነት ተገንብቶ ይጠናቀቃል።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!






Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: